Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል- ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡
 
ብልጽግና ፓርቲ 1ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በሐዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
 
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው ጉባኤው ላይ 1 ሺህ 116 የሚሆኑ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
 
የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፥ ፓርቲው በአንደኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ያስቀመጣቸውን ውሳኔዎች በመፈጸም ረገድ በርካታ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
 
ከጉባኤው ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሶስተኛ ዙር የተቀሰቀሰውን ጦርነት ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው፥ ፓርቲው እነዚህን ፈተናዎች በድል በመሻገር አገርን ከፍ ያደረጉ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል፡፡
 
ለአብነትም በጉባኤው “ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጭ መላክ አለባት” የሚል ውሳኔ መቀመጡን ጠቅሰው፤ በዘንድሮው ዓመት ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን ለወጪ ንግድ ማቅረብ ትጀምራለች ብለዋል፡፡
 
ከዚህ አኳያ በፓርቲው 1ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ገቢራዊ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ስኬት ማስመዝግብ እንደሚቻል ትምህርት የሰጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
 
ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በርካታ አባላትን በመያዝ ግን በአህጉር ዓቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ፓርቲው በአፍሪካ በህዝብ ቁጥር ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት ተረታ የምትሰለፍ ሀገር እየመራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በቀጣይ በርካታ ስራዎች ይጠበቁበታል ነው ያሉት፡፡
 
ለዚህ ደግሞ እውቀትና ክህሎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እርስ በርስ በመደማመጥ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ የማደግ ተስፋ ያላት ታላቅ ሀገር መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ ለኢትዮጵያ የእድገት ጉዞ እንቅፋት የሆኑ ትርክቶችን መቅረፍ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
 
በተለይ ያለፉ ታሪኮች የግጭትና መለያየት ምንጭ መሆን እንደሌለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
 
ከትናንት ታሪኮች ትምህርት በመውሰድ እንዳይደገሙ መስራትና የተሻለ ነገን ለመገንባት በጋራ መቆም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
 
ያጋጠመንን ጦርነት በተቀናጀ መንገድ በጋራ መመከት እንደቻልን ሁሉ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥም የበኩላችንን ሚና ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
 
ሌብነት ላይ የተጀመረው ትግልም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
 
በቀጣይም የፓርቲው አባላት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች እንዲሳኩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
 
በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ፓርቲው በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
 
ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በበኩላቸው÷ ፓርቲው ያካሄደውን አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ተከትሎ ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
 
በተለይ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ከጊዜያዊ መፍትሄ ባሻገር እንደ ስንዴ ልማት ባሉ ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ከፍተኛ ስራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡
 
የፓርቲውን ውስጠ-ዴሞክራሲ የሚያጠናክሩ ስራዎችን በማከናወን ረገድም የተሻለ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
 
ብልጽግና ፓርቲ ለዴሞክራሲ ተቋማት መጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ፓርቲው በአስቸኳይ ጉባኤው የምርጫ ቦርድ የሰጠውን የማስተካካያ ሃሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.