Fana: At a Speed of Life!

በበረራ ደህንነት ዘርፍ እየተሰጠ የሚገኘው አገልግሎት በአስተማማኝ የበረራ ደኅንነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ደህንነት ዘርፍ እየተሰጠ የሚገኘው አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውና በአስተማማኝ የበረራ ደኅንነት ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የአሜሪካ ትራንስፖርት ደህንነት መስሪያ ቤት የኦዲት የልዑካን ቡድን ገልጿል።

የአሜሪካ ትራንስፖርት ደህንነት መስሪያ ቤት (TSA) የኦዲት የልዑካን ቡድን ለአምስት ቀናት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያከናወነውን አጠቃላይ የበረራ ደህንነት (የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ) ኦዲት ስራ አጠናቋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በቆይታው የበረራ ደህንነት (የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ) ዘርፍ የሚያከናውናቸውን የመንገደኞች፣ የሻንጣ፣ የካርጎ ጭነት፣ እንዲሁም የአውሮፕላን ፍተሻ፣ ደህንነት አጠባበቅና ቁጥጥር እንዲሁም የእጀባ ስራ ተመልክቷል።

በዚህም አጠቃላይ አሰራርና የቅድመ መከላከያ ዘዴ አተገባበር ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑና ከአለም ዓቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የተወሰዱና የበረራ ኢንዱስትሪው የሚገለገልባቸውን የተለያዩ ሰነዶች ከአተገባበር አንፃር የማመሳከርና በጥልቀት የመመርመር ተግባር አከናውኗል፡፡

እየተከናወነ የሚገኘው ስራ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር ተምሳሌት መሆኑንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ለደረሰበት ከፍታ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የበረራ ደህንነት ዘርፉ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስታውቋል፡፡

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጀላ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ የበረራ ደህንነት ዘርፍ እና በአየር መንገዱ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሌት ተቀን በጋራ በመስራታቸው ኦዲቱን ያለምንም ግኝት በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል።

ይህም ውጤት መገኘት ለሀገራችን የአቬየሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.