Fana: At a Speed of Life!

ለደቡብ ክልል 400 የውኃ መሳቢያ ፓምፖችን ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ሚኒስቴር ለበጋ መስኖ ልማት አገልግሎት የሚውሉ 400 የውኃ መሳቢያ ፓምፖችን ለደቡብ ክልል ድጋፍ አድርጓል።

የውኃ መሳቢያ ፓምፖቹን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ አስረክበዋል፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት÷ የውኃ መሳቢያ ፓምፖቹ በክልሉ ከ200 ሺህ ሔክታር በላይ መሬትን በተቀናጀ መንገድ በመስኖ ለማልማት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ያግዛሉ፡፡

ከዚህም ውስጥ 20 ሺህ ሔክታሩ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚሸፈን መሆኑን እና ሚኒስቴሩ ለዚህ ወሳኝ ልማት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥትም ለዘርፉ ስኬታማነት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መደቦ እየተቀሳቀሰ ነው ማለታቸውን የደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው÷ ሚኒስቴሩ በዘርፉ በራሱ ከሚሠራቸው ተግባራት ባሻገር በክልሎች ታላላቅ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ዘርፉን ለማጎልበት ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.