Fana: At a Speed of Life!

በዓባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ኅጎች እና ሥምምነቶች ተገዢ ናት – በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ኅጎች እና ሥምምነቶች በቁርጠኝነት እንደምትገዛ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር አስታወቁ፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ የሚካሄዱ ማናቸውም ዓይነት የሌሎች የወንዙ ተጠቃሚ ሀገራት ስምምነቶች እንደማትገዛም ነው ያስገነዘቡት፡፡

አምባሳደሩ በዓለምአቀፍ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ አጠቃቀም ኅግ ፣ የውሃ ፖለቲካ እና የውሃ ዲፕሎማሲ ላይ በፓኪስታን ኢስላማባድ በተዘጋጀ ዐውደ ጥናት ላይ ጥናታዊ ፅሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡

በዐውደ ጥናቱ ላይ አምባሳደር ጀማል በከር ÷በዓባይ ጉዳይ ኢትዮጵያን ባሳተፈው በፈረንጆቹ 1999 ላይ በተካሄደው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኢኒሼቲቭ በቀጥታና በንቃት መሳተፏን አስታውሰዋል፡፡

ፍትሃዊ ፣ አካታች እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የዓባይን ወንዝ ጥቅም ላይ በማዋል ዘላቂነት ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማስመዝገብ ፎረሙ መምከሩንም ነው ያወሱት፡፡

በዓለም ባንክ ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ፣ እና በሌሎች ለጋሾች በመታገዝ የትብብር ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የሥምምነት ረቂቁ ላይ ከዐሥር ዓመታት በላይ ሰፊ ድርድር ተካሂዷልም ብለዋል፡፡

ረቂቅ ስምምነቱም በዓባይ ወንዝ ላይ የአንድን ሀገር የበላይ ተጠቃሚነት ያስቀረና የአካባቢው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ሥነ-ምኅዳሩን በጠበቀ መልኩ እንዲሁም የትብብር መርኅን እና የመጋራት ግዴታን የጣለ እንደነበርና ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ ያደረግ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ ከዓባይ ወንዝ እና ከታላቁን የኅዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ከግብፅ እና ከሱዳን የሚነሱ የኅግ ጥያቄዎች ለመመለስ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እና ነፃ ሳይንሳዊ የምርምር ቡድን በማቋቋም ሳይንሳዊ ጥናቶችን ላይ የተመሰረቱ እና የመተማመን ስሜትን የሚያዳብሩ ወሳኝ እርምጃ ወስዳለችም ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የዓለም አቀፉን የውሃ ኅጎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የድንበር ተሻጋሪ የውሃ አጠቃቀም ኮንቬንሽን እና የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ የውሃ ኅጎች ላይ የወጡ የተለያዩ መርኅዎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተተገበረ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በአፍሪካ ትልቁ እና ከዓለም በ10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ በሥነ-ምኅዳርም ሆነ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ የማያደርስ ንፁህ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

በዐውደ ጥናቱ ላይ አምባሳደሩ የውሃ ፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ርዕሰ ጉዳዮች ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት የነበራቸውን ሂደት ማብራራታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከፓኪስታን ኢኮኖሚክ ኔትወርክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር በዓለም አቀፍ የውሃ ኅጎች እና ስምምነቶች እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተፋሰስ ኮንቬንሽን እና የጋራ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሐብቶች አጠቃቀም ላይ ንድፈ ሐሳቦችን ለዐውደ ጥናቱ ታዳሚዎች ማቅረባቸውም ነው የተመለከተው፡፡

በዓለማችን ዙሪያ ከሚገኙት ወንዞች እና ሐይቆች ሦስት አራተኛ ያህሉን በዓለምአቀፉ የተፋሰስ ሀገራት ኅግ መሠረት በመጋራት የሚጠቀሙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ከ270 የሚበልጡ ተፋሰሶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ተፋሰሶቹም ወደ 40 በመቶ ለሚሆነው የዓለም ሕዝብ ንፁህ ውሃ በማቅረብ ረገድ የማይናቅ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኙ ነው በጥናታዊ ፅሑፋቸው ያስረዱት፡፡

የአባይ ወንዝ ፣ ኢንዱስ፣ ጋንጌስ፣ ኤፍራጥስ -እና ቲግሪስ እንዲሁም ሜኮንግ ደግሞ የማይናቅ ሚና እያበረከቱ የሚገኙ ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.