Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በሽብር፣ በጽንፈኞች፣ በሌብነትና የጥቅም ትስስሮች ላይ የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ ይቀጥላል- ዶ/ር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በሽብር፣ በጽንፈኞች፣ በሌብነትና የጥቅም ትስስሮች ላይ የጀመረውን ዘመቻ እና እርምጃ ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፥ ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያጋጠመውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ወደሚያስችለው የሰላም ስምምነት ተሻግራ የሚጠበቅባትን ሁሉ እየተወጣች ትገኛለች ብለዋል።

ይህ የሰላም ጥረት እረፍት የነሳቸው የሽብር፣ የጽንፈኛ እና ለሌብነት ዓላማ የተሳሰሩ ቡድኖች በተናጠል እና በቅንጅት በአክራሪ ሚዲያዎች ታግዘው በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በወለጋ አንዳንድ ቦታዎች ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ንፁሃን ዜጎችን ገድለዋል፤ አፈናቅለዋል፤ በፀጥታ ሃይሎቻችን ላይ ጉዳት አድርሰዋል፤ የግለሰቦችንና የመንግስት ንብረት አውድመዋል ነው ያሉት።

ይህን እኩይ ድርጊታቸውን የትምህርት ተቋማትን ማዕከል ባደረገ አግባብ ወደ አዲስ አበባም ለማስፋፋት ከሰሞኑ አልመው እየሰሩ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ፥ የኦሮሞና የዐማራ ወጣት እርስ በርስ እንዲፋጅ በየፊናቸው ለዚሁ ዓላማ ባደራጁት ሚዲያ በገሀድ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ህግን መሠረት አድርገው የተደራጁ ሃይሎችም ይህንን ጉዳይ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ እያስተጋቡ መሆኑን እየታዘብን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የእነዚህ የሽብርና የጽንፈኝነት ሃይሎች ዋና ዓላማ መንግስት በሌብነት ላይ የከፈተው ዘመቻና በሰሜኑ የተጀመረው የሰላም ጥረት ከዳር እንዳይደርስ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

ማንነትን ማዕከል በማድረግ እርስ በርስ ተቃራኒ መስለውና ይህንኑ ድርጊት በጽንፈኛ ሚዲያዎች እና ማህበራዊ አንቂዎች ታግዘው የሆነ የማህበረሰብ ክፍል በተለየ መንገድ እንደተጠቃ በማስመሰል ከየራሳቸው አኳያ እያስተገቡ በተጨባጭ ተግባር ደግሞ እኩይ ድርጊቱን በተናበበና በተቀናጀ መንገድ ይፈጽማሉ ።

ሰሞኑን በወለጋ አንደንድ ቦታዎች የታየው ይህ እውነታ ነው፤ በዚህም ህብረተሰቡ ግራ እንዲገባና በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ ይሰራሉ፤ አራቱም ሃይሎች በጥቅም የተሳሰሩ ፣ ከብጥብጥና ሁከት ውጭ ዓላማቸው የማይሳካ ፣ እኩልነትን የማይቀበሉ እና ሰላም ጠል ናቸው ነው ያሉት ዶክተር ለገሰ።

መንግስት በሽብር፣ በጽንፈኞች፣ በሌብነትና የጥቅም ትስስሮች ላይ የጀመረውን ዘመቻ እና እርምጃ ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፥ እስካሁን የተገኙ ውጤቶችም አበረታች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ጥያቄዎቻቸውን በውይይት፣ በድርድር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚፈልጉ ሃይሎችም በሩ ክፍት ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች ከልዩ ልዩ አሉባልታዎችና ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ራሱን በመጠበቅ፣ አንድነቱን በማጠናከር በሽብርና ጽንፈኛ ቡድኖች እንዲሁም በሌብነት ላይ መንግስት የጀመረውን ዘመቻ መደገፍ እና ማገዝ ይኖርበታል ነው ያሉት።

የትኞቹም ሚዲያዎች ህብረተሰቡን ጥላቻ ላይ ወደተመሠረተ ግጭት ከሚያስገቡ ቅስቀሳዎች መቆጠብ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል፡፡

ከዚህ አልፈው በሚሄዱት ላይም ለመላው ደህንነት ሲባል ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልፀዋል፡፡

የመላ ህዝባችን ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ከዘላቂ ሰላም ፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ ከእኩልነትና ከጋራ ልማት ነዉ፤ ለዚህ መርህ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከዋልታ ረገጥ ፖለቲካ መጠቀም የሚችሉት በጥቅም ትስስር ውስጥ ያሉ ጥቂት ግለሰቦች ናቸው ሲሉም አስፍረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.