Fana: At a Speed of Life!

ኤርትራ እና ኬንያ በንግድ ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ያለ ቪዛ በሀገራቱ መንቀሳቀስ በሚቻልባቸው ማዕቀፎች ላይ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ኤርትራ እና ኬንያ በንግድ ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ያለ ቪዛ በሀገራቱ መንቀሳቀስ በሚችሉባቸው ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸው ተገለጸ፡፡

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነትን ጨምሮ በቀጠናዊ እና በሌሎች ጉዳዮቻቸው ላይ በትብብር ለመሥራት መሥማማታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል፡፡

ኤርትራ እና ኬንያ ቀጠናዊ ውኅደትን ዕውን ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ነው የተመለከተው፡፡

ሀገራቱ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የፓን አፍሪካ መንፈስ ለማንጸባረቅ እንደሚተባበሩም ተገልጿል።

ቀጣናዊ ሠላም እና ፀጥታ ለማረጋገጥ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ልማት ዕውን ለማድረግ በጥምረት እንደሚሰሩም ነው በመረጃው የተጠቆመው፡፡

የሀገራቱ መሪዎች የባሕር እና የዓየር የትራንስፖርት አማራጮቻቸውን በማልማት ቀጠናዊ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳለጥ እና የኢንቨስትመንት አማራጮቻቸውን ለማየት መክረዋልም ነው የተባለው፡፡

ወቅታዊ ተግዳሮቶቻቸውን ለመፍታትም ቀጠናዊ ውጥኖቻቸውን በመቃኘት ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ እና ሐብት ማሰባሰብ ላይም በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኤርትራ መግባታቸው ይታወሳል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.