Fana: At a Speed of Life!

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ እስካሁን 6 ሀገራት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞቻቸውን አሰናብተዋል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ሥድስት ሀገራት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞቻቸውን ሲያሰናበቱ የአሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት ውሳኔ ተጠባቂ ሆኗል፡፡

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ከተሳተፉ 32 ሀገራት መካከል ውጤት ያልቀናቸው ሥድስት ሀገራት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝኞቻቸውን አሰናብተዋል፡፡

የቤልጂየሙ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ፣ የጋናው ኦቶ አዶ የደቡብ ኮሪያው ፓውሎ ቤንቶ፣ የሜክሲኮው ጀራርድ ማርቲኖ፣ የስፔኑ ሎዊስ ኤነሪኬ እና የብራዚሉ ቲቴ በዓለም ዋንጫው ከኃላፊነታቸው የተሰናበቱ አሰልጣኞች ናቸው፡፡

እንግሊዝ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ትናንት ምሽት በፈረንሳይ ተሸንፋ ከውድድሩ ውጭ መሆኗን ተክትሎ የአሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት የብሔራዊ ቡድን ቆይታ ውሳኔ ደግሞ ተጠባቂ ሆኗል፡፡

አሰልጣኙ ከትናንት ምሽቱ ጨዋታ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ “የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ቆይታዬን ለመወሰን ጊዜ ወስጄ ማሰብ ይኖርብኛል” ብለዋል፡፡

“በዓለም ዋንጫ ቆይታዬ እረፍት አልነበረኝም” ያሉት የእንግሊዙ አለቃ፥ “ቆይታዬን በተመለከተ ቡድኑን የሚጠቅመውን እና ትክክለኛውን ውሳኔ ማሳለፍ ይኖርብኛል” ብለዋል፡፡

ሳውዝጌት ከእንግሊዝ ብሐየራዊ ቡድን ጋር ያላቸው ኮንትራት እስከ 2024 ድረስ የሚቆይ ሲሆን፥ በቡድኑ የሚቆዩ ከሆነ በጀርመን አዘጋጅነት በሚካሄደውን የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ሦስቱን አናብሰቶች ይመራሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.