Fana: At a Speed of Life!

ሑመራ በድጋሚ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አገኘች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባት የቆየችው የሑመራ ከተማ ዛሬ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል በድጋሚ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በአገልግሎቱ የጎንደር ዲስትሪክት ዳይሬክተር ሞገስ አበራ እንደገለጹት÷ ከተማዋ አገልግሎቱን ያገኘችው ከሑመራ፣ ማይካድራ፣ አብድራፊ፣ አብረሃጅራ፣ ከሑመራ-ባከር-ዳንሻ እና ከሑመራ-አዲጎሹ ባሉ ሦስት አቅጣጫዎች የዝቅተኛ እና መካከለኛ የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ሥራ አስቀድሞ በመጠናቀቁ ነው፡፡

ከሑመራና ሽረ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ ያገኙ የነበሩት ዳንሻ፣ በአከር፣ ማይካድራ፣ አብደራፊ፣ አብራጅራ፣ ሶሮቃ፣ አዲ ጎሹ፣ አዲ ረመፅ፣ አዲዓርቃይ፣ ኢንዳባጉና፣ አዲገብሩ ከተሞችና በርካታ ቀበሌዎች በቀጣይ ተጠቃሚ ይሆናሉ ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም የሑመራ – ሽረ 230 ኪሎ ሜትር ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር ጥገና እና የተከዜ መስመር ጥገና በመጠናቀቁ ለሑመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ማድረስ መቻሉን ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡

በመሆኑም ከሑመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ያገኙ የነበሩ ከተሞች በሙሉ ኃይል የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩ ተገልጿል፡፡

በቀጣይም ኃይል ያላገኙ አካባቢዎችን መልሶ ለማገናኘት በትኩረት እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.