Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ፑቲን ከቱርክ አቻቸው ኤርዶኻን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቱርክ አቻቸው ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ በስልክ ተወያዩ።

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በተለይም በኃይል፣ በምግብ እህል አቅርቦት፣ ሽብርተኝነትን በጋራ በመዋጋት እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

እስካሁን በጋራ በተሠራ ሥራ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካላት በቱርክ የእህል ማስተላለፊያ ኮሪደር በኩል ከ13 ሚሊየን ቶን በላይ እህል ማቅረብ መቻሉን እና ሌሎች የምግብ ዓይነቶችንም በይፋ ለማስተላለፍ መሥራት እንደሚቻል ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን ገልጸዋል፡፡

በሂደትም ሌሎች ሸቀጦችን ማስተላለፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሥራት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የሩሲያ ዩክሬን ግጭት በተቻለ ፍጥነት እንዲያበቃ ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን መመኘታቸውን ከጽሕፈት ቤታቸው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ተገንጣይ የሽብር ቡድኖችም ከሰሜናዊ ሶሪያ በመነሳት ቱርክ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈፀም መቀጠላቸውን ጠቁመው፥ በፈረንጆቹ 2019 በተደረሰው ስምምነት መሰረት አሸባሪዎችን ማፅዳት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.