Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅታዊ የከተማዋ ጉዳዮች ዙሪያ ከነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅታዊ የከተማዋ ጉዳዮች ዙሪያ ከነዋሪዎች ጋር ተወያዩ።

ከንቲባ አዳነች በወቅታዊ የመዲናዋ ጉዳይ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማካሔዳቸውን ገልፀዋል።

“በከተማችን በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ባንዲራ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ ያጋጠሙንን የፀጥታ መደፍረስ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ዛሬ በግልፅ ተወያይተናል” ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ በአፋን ኦሮሞ እንማር የሚለው ጥያቄ በከተማዋ ከተጀመረ አምስት ዓመታት ማስቆጠሩን ገልጸዋል፡፡

ጥያቄው በለውጡ ዋዜማ (በዘመነ ኢህአዴግ) መጀመሩን ጠቁመው፥ በወቅቱ የኦሮሚኛ ቋንቋን ለማስተማር ሲፈለግ ለዚህ የሚሆን ስርዓተ ትምህርት የአዲስ አበባ ከተማ ስላልነበራት የቋንቋው ማስተማሪያ ሥርዓተ ትምህርት ከኦሮሚያ ክልል በውሰት መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ እንደተቀመጠው በኦሮሚኛ ቋንቋ ትምህርት ሲሰጥ የክልሉ ባንዲራ እንዲሰቀልና የክልላዊ መንግሥቱ መዝሙር መዘመርን አያይዞ በአንድ ላይ እንደ ሕግ የሚያስቀምጥ በመሆኑ÷ ይህ ሁኔታ ትምህርቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎችም ሁሉ ላለፉት ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጅ በአንዳንድ አካላት ዛሬ እንደተጀመረ አስመስሎ በማቅረብና የአንድን ክልል ባንዲራና መዝሙር በተለየ ሁኔታ በግድ ለመጫን እንደተደረገ አስመስለው በማቅረብ እየፈጠሩት ያለው ውዥንብር ትክክል አለመሆኑን ከህብረተሰቡ ጋር በግልፅ ተማምነናል ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ሆኖም ይህ አጀንዳ ከአንድ ዓመት በፊት ለአዲስ አበባ ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት መሰረት አዲስ አበባ አሮሚኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በሶማሊኛ እና ጋሞ ቋንቋም ማስተማር ስለጀመረች እና ተጨማሪ ቋንቋዎችንም ለማስተማር የጀመረችው የሥርዓተ ትምህርት ጥናት በመጠናቀቁ፥ ይህ የግጭት አጀንዳ መሆን የለበትም በሚል ቀርቦ ሃሳብም ተሰጥቶበት እንደነበር ነው የጠቆሙት።

“አሁንም በምክር ቤቱ ላይ ቃል ገብተነው እንደነበረው ለአዲስ አበባ የተዘጋጀውን የቋንቋዎች ሥርዓተ ትምህርት ጥናቱን አጥንተን ያጠናቀቅን እና ወደ ውሳኔ እየመጣን በመሆኑ÷ ህብረተሰቡ እና የትምህርት ማህበረሰቡ በእርጋታ ከጥፋት ኃይሎች ሴራ ራሱን እየጠበቀ እንዲቆይ ለማሳሰብ እወዳለሁ” ብለዋል።

በተለይም አምስት ዓመታትን የቆየ አጀንዳ ልክ ዛሬ የለውጥ አመራሩ ያመጣው በማስመሰል እና አንዱ ብሔር በሌላው ላይ የበላይነት ለማምጣት እየተሠራ እንዳለ በማስመሰል የሚቀርበው ሐሳብ ፍፁም የተሳሳተ፣ ፅንፈኛ እና አሸባሪ ኃይሎች፤ በዚህ አጀንዳ ከተማችንን ለማተራመስ እየሠሩት ያሉት ጉዳይ መሆኑንም ከውይይቱ ተሳታፊዎች ጋር መስማማታቸውን ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን ማንኛውንም አይነት ጥያቄ እና ሐሳብ በመመካከር እና በውይይት እንጂ በሁከት እና በትርምስ መሆን እንደሌለበትም መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

በመሆኑም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይስተጓጎል እና የከተማችን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ግባችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እነዚህን የግጭት ነጋዴዎች አጋልጦ የመስጠት ሥራ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

መንግሥትም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር፣ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ እና የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።

ተማሪዎች ለጥያቄው በሕጋዊ አካሄድ ምላሽ እንደሚሰጥ አውቀው እስከዛው ድረስ መላው ትኩረታቸውን ሰብስበው ትምህርታቸው ላይ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

“መንግሥታዊ ኃላፊነታችንን የሕዝባችንን ስሜት እና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ሁሉንም ጉዳዮች በቅርበት ከሕዝቡ ጋር እየተመካከርን መወጣታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ነው ቃል የገቡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.