Fana: At a Speed of Life!

ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ የመልሶ ማቋቋም ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም ድጋፉ በቂ አይደለም ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግጭቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው በመመለስ መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም ከደረሰው ጉዳት እና ከተጎጂዎች ቁጥር አኳያ የሚደረገው ድጋፍ በቂ አለመሆኑ ተገለጸ፡፡

በራያ ቆቦ ወረዳ እንዲሁም በቆቦ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞች ነዋሪዎችን መልሶ የማቋቋምና አገልግሎቶችን ዳግም የማስጀመር ሥራ ቢጀመርም እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡

የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ ሞላ ደሱ፣ የቆቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሰዒድ አባተ፣ የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኃይሉ አበራ እንዲሁም የኮረም ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰላም ደበሳይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሮቹ የስራ ኃላፊዎች እንዳስታወቁት÷ ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው በመመለስ መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም እየቀረበ ያለው የድጋፍ መጠን እና ዓይነት ግን በቂ አይደለም፡፡

ከደረሰው የጉዳት መጠን እና ድጋፉ ከሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አኳያ እየቀረበ ያለው ድጋፍ መጠን እና የሚደገፉ ሰዎች ቁጥር አሁን ካለበት ከፍ እንዲልም ጠይቀዋል፡፡

እየቀረበ ያለው ድጋፍ በዓይነትም ሆነ በመጠን በቂ ባለመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እንዲቀርብላቸውም ነው የጠየቁት።

ከዚህ ባለፈም ከምግብ ነክ ድጋፍ በተጨማሪ የትምህርት፣ የቤት እና የቢሮ ቁሳቁስ እገዛ እንዲደረግ የአስተዳደሮቹ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው እጥረት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው÷ እጥረቱን ለመቅረፍ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ድጋፉ አሁንም ተደራሽ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ደበበ÷ ለዚህም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እየቀረበ ያለውን ድጋፍ የሚከታተል ሦስት ቡድን ወደ ሥፍራው መላኩን አመላክተዋል፡፡

ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ሁሉንም ድጋፍ ከመንግሥት ብቻ ከመጠበቅ÷ ህብረተሰቡ፣ ተቋማት፣ ማኅበራት እንዲሁም አጋር አካላት እገዛ ቢያደርጉ እጥረቱን ማቃለል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.