Fana: At a Speed of Life!

የቄስ በሊና ሠርካ ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቄስ በሊና ሠርካ ስርዓተ ቀብር በአዲስ አበባ በጴጥሮስ ወጳውሎስ የፕሮቴስታንት እና ካቶሊክ መካነ መቃብር ተፈፀመ፡፡

በቀብር ሥነስርዓቱ ላይ ቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የሐይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ቄስ በሊና ሠርካ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተዉ ሕዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ማረፋቸው ይታወሳል፡፡

ቄስ በሊና ሳርካ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ አገልጋይ እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

በቤተክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የአገልግሎት ታሪክ ያላቸውን ትጉህና ታማኝ አገልጋይን በማጣቷ የቤተክርስቲያኒቱ አመራርና ምዕመናን የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል፡፡

በሽኝት መርሐ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ቄስ በሊና በትውልድ ላይ መልካም ዘርን የዘሩ፣ ፍቅርን መከባበርን፣ መሥራትን በምድር ላይ በተሰጠቻቸው ጊዜ ያስተማሩ አባት ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።

ቄስ በሊና በሕይወታቸው የተናገሩትን በመኖር፣ለእውነት በመቆም መለወጥ እንደሚቻል እና ለእውነት ዋጋ መክፈል እንደሚገባ ራሳቸው ህያው ምስክር ሆነው መኖራቸውን አውስተዋል፡፡

ከእሳቸው በመማር በእውነት፣ በአንድነት እና በጽናት እንቁም ሲሉም አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.