Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ክንውን እንዲኖረው የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሳስ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ ክንውን እንዲኖረው የሚረዳ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
 
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በምክክር ሂደቱ ተሳትፎና በአጀንዳ አሰባሰብ አሰራር ዙሪያ ከኃይማኖት ተቋማት፣ አካል ጉዳተኞች ማህበራት፣ የወጣቶችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።
 
የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ ሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነትና ጽንሰ ሀሳቡ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጹሁፍም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
 
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ÷ ኮሚሽኑ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚደረገውን ዝግጅት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
 
ኮሚሽኑ ስራውን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማከናወን ከሃገር ሽማግሌዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃንና ክልሎች ጋር ውይይት በማድረግ በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶችን ወስዷል ብለዋል።
 
በአሁኑ ወቅትም በቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል ደረጃ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ÷ለዚህም የሚጠቅም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
 
በምክክር ሒደቱ በአንድ ግዜ በርካታ ወረዳዎችን ተደራሽ ማድረግ ስለማይችል የሂደቱን ተደራሽነት እውን ማድረግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እንደተዘጋጀ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለሥራው መቀላጠፍ የሚያግዙትን ጽህፈት ቤቶች በዩኒቨርሲቲዎች ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑም ጠቅሰው÷ ከሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት ተካሂዶ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
 
በአዲስ አበባ የካና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መላከ ምህረት ዘካሪያስ፤ የሰው ልጆች በፍቅርና በአንድነት መኖር እንዳለባቸው የፈጣሪ አስተምህሮ ማዘዙን አመልክተው ለምክክርና አብሮነት ሁላችንም ከልባችን ልንዘጋጅ ይግባል ብለዋል።
 
የአረጋዊያን ማህበርን ወክለው የተገኙት ጌታቸው ዘውዴ÷ ኮሚሽኑ የሚሰጠንን ኃላፊነት ተቀብለን ለተግባራዊነቱ ለመስራት ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.