Fana: At a Speed of Life!

በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተርና አራት ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሳሥ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር በሆኑት ተስፋዬ ደሜ እና አራት የአገልግሎቱ ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ተገለጸ።
የስራ ሀላፊው እና ባለሙያዎች ላይ ክስ የተመሰረተው በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ስም 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ከሁለት ፋብሪካዎች ገዝተው ለግለሰቦች በመሸጥ ከ30 ሚሊዬን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው በማዋል የተጠረጠሩ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ተከሳሾቹም 1ኛ ተስፋዬ ደሜ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር፣ 2ኛ አሸናፊ ተስፋዬ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ዋና ክፍል ሃላፊ፣ 3ኛ ቱጅባ ቀልቤሳ እና 4ኛ ተከሳሽ ሙስጠፋ ሙሳ የግዢ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውን አስታውቋል።
ተከሳሾቹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2013 እና 2014 ዓ.ም በተለያዩ ወራት በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምንም አይንት ሲሚንቶ ግዢ ባልተፈፀመበት ሁኔታ በስሙ ሲሚንቶ ከፋብሪካዎች በአነስተኛ ዋጋ በመግዛትና ገበያ ላይ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ መጠርጠራቸውን ገልጿል።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ አገልግሎቱ የሲሚንቶ ግዢ ፍላጎት ሳይኖረው እንዳለው በማስመሰል ለአገልግሎቱ አስቸኳይ የግንባታ ስራ የሚውል በድምሩ 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ሽያጭ ከደርባና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲፈፀም ማድረጋቸው ተጠቅሷል።
የስራ ሀላፊው በ3ኛ እና በ4ኛ ተከሳሽ ስም ደብዳቤዎችን በመፃፍ፣ በተከሳሾች የግል አካውንት ገቢ በማድረግ፣ ወደ ፋብሪካችሁ ገቢ በሆነው ገንዘብ ለመስሪያ ቤታችን የሲሚንቶ ሽያጭ እንድትፈፀሙ በማለት ደብዳቤ በመፃፍ በመስሪያ ቤቱ ስም ግዢ እንዲፈፀም እና ሲሚንቶው ወደ መስሪያ ቤቱ ገቢ ሳይደረግ አየር ላይ ተሸጦ ለግል ጥቅሙ እንዲውል ያደረገ በመሆኑ፤
2ኛ ተከሳሽም 1ኛ ተከሳሽ ያለምንም ግዢ ፍላጎት በተቋሙ ስም ግዢ እንዲፈፀም የፃፋቸውን ደብዳቤዎች 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ለደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲያደርሱ እና ተከሳሾች በግል አካውንታቸው ገቢ በሚያደርግላቸው ገንዘብ ከየፋብሪካዎቹ የሲሚንቶ ግዢ እንዲፈፅሙ በመንገርና ደብዳቤዎቹን በመስጠት በተቋሙ ስም የተገዛውን 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው እንዲውል ያደረገ በመሆኑ፤
3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ ለደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በተቋሙ የሲሚንቶ ግዢ ፍላጎት ሳይኖር ለደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ3ኛ ተከሳሽ ስም 7 ሺህ 200 ኩንታል፣ በ4ኛ ተከሳሽስም 22 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ፣ በድምሩ 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ግዢ እንዲፈፀም በተፃፈ የተቋሙ ደብዳቤ አማካኝነት በግል አካውንታቸው በሚገባ ከፍተኛ ገንዘብ ግዢ በመፈፀም ሲሚንቶው ወደ ተቋሙ ገቢ ሳይሆን አየር በአየር በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው እንዲውል ያደረጉ በመሆኑ፤
በአጠቃላይ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ምንም አይነት የግዢ ፍላጎት ሳይኖር በአገልግሎቱ ስም በፃፏቸው ደብዳቤዎች ከዳንጎቴ እና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድምሩ 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመግዛት ወደ ተቋሙ ገቢ ሳያደርጉ ገበያ ላይ በመሸጥ 30 ሚሊዬን 99 ሺ 360 ብር ጥቅም ያገኙ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ በችሎት ደርሷቸው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን፥ ተከሳሾችም የክስ መቃወሚያ ካላቸው በጽሁፍ እንዲያቀርቡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎትም ለታህሳስ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ትዕዛዝ መስጠቱን የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ተከሳሾች ላይ ክስ ስለመመስረቱ ለማሳወቅ የቀረበ ሲሆን፥ የተከሳሾችን ከፍርድ በፊት እንደ ንፁህ የመገመት ህገ-መንግስታዊ መብትን ያከብራል ሲል ባወጣው መግለጫ አሰታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.