Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ስኬት ስልጣኔን ከምድራችን ስነ ምህዳር ጋር አስታርቆ ለማስኬድ ዓለምን እንደሚያነሳሳ ምንም ጥርጣሬ የለንም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ የስኬት ታሪክ ስልጣኔን ከምድራችን ስነ ምህዳር ጋር አስታርቆ ለማስኬድ ዓለምን እንደሚያነሳሳ ምንም ጥርጣሬ የለንም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

“አፍሪካ፥ የዓለም አቀፍ ንቅናቄ አጣዳፊነት” በሚል መሪ ሀሳብ “አሜሪካን አካዳሚ ኦፍ አቺቭመንት እና ግሎባል ሆፕ ኮአሊሽን” የተሰኙት ተቋማት በዋሽንግተን ዲሲ በጋራ ባዘጋጁት ልዩ ዝግጅት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄን አስመልክቶ ላሳዩት አመራር “የአፍሪካ የላቀ አመራር” ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፥ ዓለም የዓየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅእኖዎች ጋር ሲታገል ኢትዮጵያ ተግባራዊ እና የሚታይ መፍትሄን መርጣ መስራት ጀምራለች።

በአውሮፓውያኑ 2019 ላይ መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለፈም ቢሆን፥ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ ተንቀሳቅሰው ሀገራቸውን አረንጓዴ ለማልበስ ችግኝ ይዘው መነሳታቸውን አስታውስዋል።

በኢትዮጵያ ከሰኔ እስከ ነሃሴ ወራት የዝናብ ወቅት መሆኑን፣ ከዘጠኝ ወራት የፀሃይ ወቅት በኋላ አቧራ የሚያፍብት አፈር የሚረሰርስበት ለችግኝ ተከላ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት መሆኑን አስረድተዋል።

በእነዚህ ሶስት ምቹ ወራትም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዜጎች ከቤታቸው፣ ከስራ በታቸው ነቅለው በመውጣት ችግኝን እንዲተክሉ ማስቻሉን ነው የጠቆሙት።

በአራት ዓመት ትግበራውም 25 ሚሊየን ዜጎችን ማንቀሳቀስ የቻለው ዘመቻው፥ 25 ቢሊየን ችግኞችን መትከል አስችሏል ብለዋል፤ ይህም ማለት የበካይ ጋዝ ወደ ከባቢ ዓየር የሚለቁ 64 ሚለየን ተሽከርካሪዎችን ለአንድ ዓመት ከመንገድ ዞር እንደማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአማዞን ቀጥሎ የዓለም ትልቁ የደን ልማት ንቅናቄ መሆኑን በመጠቆም፥ ሀገሪቱ ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ 700 ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ደን በዘላቂነት ተጠብቆ እንዲቆይ እያደረገች መሆኑን አመልክተዋል።

በፈረንጆቹ 2022 ላይ የሚተከሉ ችግኞች ቁጥር በሶስት እጥፍ ማደጋቸውን፣ ለ700 ሺህ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ ማስገኘቱን ነው በንግግራቸው የዘረዘሩት።

ኢትዮጵያ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራትም በማካፈል ትብብር እንዲዳብር እና የአካባቢው ስነ ምህዳር እንዲጠበቅ መስራቷን ተናግረዋል።

ይህ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመቶ ሚሊየን ቶን የሚቆጠር በካይ ጋዝ ከከባቢ አየር እንዲቀንስ እና በረሃማነት እንዲገታ እንደሚያስችል እርግጥ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም የዓለም ሙቀት መጨመር ለመቀነስ እና የዓየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የኢትዮጵያ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ የሚያሳይ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በሀገር ውስጥ ሀብት እየተደገፈ የመጣው ይህ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መሃ ግብር በማንኛውም መስፈርት ቢለካ አስደናቂ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፥ በፈረንጆቹ 2030 ድረስ 22 ሚሊየን ሄክታር የተጎዳ መሬት መልሶ እንዲያገግም የማድረግ እቅድ መያዟን አስታውቀዋል።

አፍሪካ የበርካታ የስኬት ታሪኮች ባለቤት መሆኗን በመጠቆምም፥ የደን መመናመንን በመግታት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ አረንጓዴ ማህበረሰብን ለመገንብት እንሰራለን ብለዋል።

“አሜሪካን አካዳሚ ኦፍ አቺቭመንት እና ግሎባል ሆፕ ኮአሊሽን” ለአህጉሪቱ ላሳዩት ወዳጅነት እና ይህን ስኬታማ ክንውን ተገንዝበው ለሰጡት ዕውቅና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመስግነዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.