Fana: At a Speed of Life!

ደም ግፊትን ያለ መድሃኒት እገዛ እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ደም ግፊትን ለመቆጣጠር ከማረጋጊያ መድሃኒት ባለፈ የአኗኗር ዘይቤን እና አመጋገብን በማስተካከል መቆጣጠር እንደሚቻል በጤናው ዘርፍ የተሰሩ በርካታ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

በዕለት ተዕለት ኑሯችን የምንከተለው የአኗኗር ዘይቤ እና የአመጋገብ ሁኔታ ደም ግፊት ከመከሰቱ በፊትም ሆነ ከተከሰተም በኋላ መቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ይወስናል።

ደም ግፊት ከተከሰተ በኋላም መቆጣጠር የሚቻልባቸው መድሃኒቶች ያሉት ሲሆን በሽታውን ያለምንም መድሃኒት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚከተሉትን መንገዶች መጠቀም ይመከራል።

ክብደት መቀነስ ፦
የጤና ባለሙያዎች ደም ግፊት ከክብደት መጨመር ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት እንዳለው ያስረዳሉ።

ክብደት ሲጨምር የመተንፈስ ችግር እንዲገጥመን ከማድረጉ በተጨማሪ ከፍ ሲልም ወደ ደምግፊት ይሸጋገራል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተመጣጣኝ የሰውነት ክብደት ቢኖርዎት ይመከራል።

ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፦
ቢያንስ በየቀኑ ለ30 ደቂቃ በቋሚነት እንደ ሶምሶማ፣ እርምጃ፣ ውሃ ዋና፣ ዳንስ እና መሰል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ደም ግፊትን የማስተካከል እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

በፈረንጆቹ 2021 የተደረገ ጥናት አንድ ሰው በቀን ከ4 ሺህ እስከ 10 ሺህ እርምጃዎች ቢራመድ መልካም እንደሆነ ያስረዳል።

ባለሙያዎች ደግሞ ከ 3 እስከ 4 ሺህ እርምጃዎችን በእግር መራመድ የደም ግፊትንም ሆነ ተያያዥ የጤና እክሎችን ለመቆጣጠር መልካም መሆኑን ይመክራሉ።

የተመጣጠነ ምግብ፦
ጥራጥሬ፣ ፍራፍሬ፣ አትክልት እና ቅባት ያልበዛባቸውን የወተት ተዋጽኦ ምግቦች እንዲሁም ስብ እና ኮሌስትሮል ያልበዛባቸውን ምግቦች መመገብ የደም ግፊትን ይቀንሳል።

ጨው መቀነስ፦
ጨው ያልበዛበትን ምግብ መመገብ ከደም ግፊት በተጨማሪ የልብ ህመም እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡

የደም ግፊት ላለባቸው ሰዎች በቀን 2 ሺህ 300 ሚሊ ግራም እና ከዛ በታች የሆነ የጨው መጠን መጠቀም በቂ ነው፡፡

አልኮል መቀነስ፦ የአልኮል መጠጥ የደም ግፊትን ከሚያባብሱ ነገሮች አንደኛው ነውና ከዛ ይራቁ።

ሲጋራ አለማጨስ፦ ሲጋራም ልክ እንደ አልኮል መጠጥ ለደም ግፊት ተጋላጭነት በመዳረግም ሆነ በሽታውን ስለሚያባብስ አለማጨስ ይመከራል።

በቂ እንቅልፍ መተኛት፦ ይህን በማድረግዎ አዕምሮንና ሰውነትን ከውጥረት በመታደግ ችግሩን መከላከል ይችላሉ።

አለመጨናነቅ፦
ከመጠን ያለፈ ጭንቀት የደም ግፊትን ሊያባበብስ ስለሚችል በተቻለ መጠን አለመጨናነቅና ዘና የሚያደርጉ ልማዶችን መከተልና ለእራስዎ በቂ እረፍት መስጠት ይልመዱ።

በየጊዜው ደምን መለካት፦ ይህን ማድረግዎ የደም ግፊት ያለበትን ደረጃ ለማወቅና ቅድመ ጥንቃቄ ለመውሰድ ያግዝወታል።

በተጨማሪም ድጋፍ እና ክትትል የሚያደርግ ሰው በአቅራቢያ እንዲኖር ማድረግ መልካም ነው።

ይህ መሆኑ ችግር ቢያጋጥምዎ እንኳን የመፍትሄ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚያግዝ የኸልዝ ላይን እና የሜዲካል ዌብ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.