Fana: At a Speed of Life!

በሚወደው የዓለም ዋንጫ ለፊት ጡንቻ አለመታዘዝ ችግር የተዳረገው ወጣት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአራት አመት አንድ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ለእግር ኳስ አፍቃሪዎች ተናፋቂውና ተወዳጅ ውድድር ነው።

በውድድሩ የሚደረጉ ጨዋታዎችም ተወዳጅነታቸው የዛኑ ያህል ነው።

አንዳንድ ተመልካቾችና የስፖርት ቤተሰቦችም ይህን ውድድር ጠብቀው ከማግኘታቸው ጋር ተያይዞ ለእያንዳንዱ ጨዋታ የሚሰጡት ግምት ከፍ ያለ ነው።

በቻይናዋ ውሃን ከተማ የሚኖረው የ26 አመቱ ቻኦ የእግር ኳስ ፍቅርና ለጨዋታዎቹ የከፈለው መስዋዕትነት ግን የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል።

ወጣቱ ቻይናዊ በዓለም ዋንጫው ምንም ጨዋታ ሊያመልጠኝ አይገባም በሚል መከታተለ የጀመረ ሲሆን፥ እስከ ጥሎ ማለፉ የተካሄዱ ጨዋታዎችን በሙሉ መከታተሉን ይናገራል።

ከስራ ውጭ ያለውን ጊዜውን በሙሉ በአራት አመት አንድ ጊዜ የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ በቴሌቪዥን መስኮት በሚወደው ስፖርታዊ ውድድር ለችግር እስከተዳረገበት ጊዜ ድረስ ተከታትሏል።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ለጨዋታው በሚል የእንቅልፍና የዕረፍት ሰአቱን መስዋዕት አድርጓል፤ ከስራ መልስ ጨዋታዎችን የሚከታተል ሲሆን፥ በዚህ ምክንያትም በቂ እንቅልፍ ማግኘት አለመቻሉ ነው የተነገረው።

ሆኖም በተከታታይ አንድም ጨዋታ እንዳያመልጠኝ በማለት እንቅልፍና የእረፍት ሰዓትን መስዋእት ማድረጉ ጤናው ላይ ችግር ያስከትላል የሚል ግምት አልነበረውም።

ምንም እንኳ ቻይና ለዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገር ባትሆንም ቻኦ አንድም ጨዋታ አያልፈኝም በሚል የወሰነው ውሳኔ ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር እርግጠኛ አድርጎታል፡፡

ከስራ እንደተመለሰ እንቅልፉንና እረፍቱን መስዋዕት በማድረግ ለተከታታይ ቀናት ሲመለከት ቆይቶ በቂ እረፍት ሳያደርግ ድጋሚ ወደስራ እንደሚገባም ነው የተነገረው፡፡

ለቀናት ደህና የነበረው ቻኦ በተከታታይ ቀናት በቂ እንቅልፍ ባለማግኘቱ ፊቱ ላይ ለውጥ መመልከት መጀመሩን ይገልጻል።

ሆኖም “ይህ ስሜት ጊዜያዊ ነው” በማለት ችላ ማለቱም ነው የተናገረው፡፡

ችላ ያለው የፊቱ ለውጥ በቂ እረፍት ካለማግኘቱ ጋር ተያይዞ ስራው ላይ ጫና ማሳደሩን አስረድቷል።

ይህ ሁኔታም ከዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በኋላ እንደተከሰተ መናገሩን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።

ሁኔታው ለውጥ ካለማሳየቱ ጋር ተያይዞም ወደ ህክምና የሄደው ወጣቱ የእግር ኳስ አፍቃሪ፥ የፊት ጡንቻ አለመታዘዝ (ፌስ ፓራላይዝ) እንዳጋጠመው ተነግሮታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ከንፈሩ ወደ አንድ አቅጣጫ መንሻፈፍ እና የአይን ሽፋሽፍቱን ማንቀሳቀስ አልቻለም።

ለዚህ ደግሞ የተጠራቀመ የእንቅልፍ እጦት፣ ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ እና ኃይለኛ ነፋስ ምክንያት መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ገልጸውለታል።

አሁን ላይም ልዩ የህክምና ክትትል እያደረገ ሲሆን፥ በቅርቡ አገግሜ ወደ ስራ እመለሳለሁ ሲል ተስፋውን ገልጿል።

የቻኦን ሁኔታ የሚከታተሉት የህክምና ባለሙያዎች የእግር ኳስ ፍቅር በልክ ይሁን ሲሉ ሌሎች ከመሰል አጋጣሚዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.