Fana: At a Speed of Life!

ከጅብሰም ጋር ተጭኖ ወደ ኬንያ ሊሻገር የነበረ 6 ሺህ 150 ኪ.ግ አደንዛዥ እፅ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ከጅብሰም ጋር ተቀላቅሎ የተጫነ 6 ሺህ 150 ኪሎ ግራም ካናቢስ የተሰኘ እፅ መያዙን የዞኑ ፖሊስ አስታውቋል።
 
አደንዛዥ እጹን የጫነው ተሽከርካሪ በኤርቦሬ መስመር በጉዞ ላይ ሳለ በበናፀማይ ወረዳ ወይጦ ወይም ብራይሌ ተብሎ በሚጠራው የገጠር ከተማ እንደደረሰ የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ባደረጉት ክትትል መያዙ ተገልጿል።
 
የተሽከርካሪው ሾፌር ንብረቱን ከጫነው ግለሰብ ጋር ከተሽከርካሪ ወርደው ያመለጡ ሲሆን÷ የተሽከርካሪውን ረዳትና ተሽከርካሪውን ከእነጭነቱ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማድረግ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
 
አደንዛዥ እፁ ከምስራቅ አርሲ ዞን ሻሸመኔ አካባቢ የተጫነ መሆኑ በምርመራ መረጋገጡን ከደቡብ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
ከኬንያና ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነው የደቡብ ኦሞ ዞን ቀጠናው የህገወጦች መፈንጫ እንዳይሆን የዞኑ ፖሊስ ከደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በመሆን ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ በመሆኑ ህገወጦች ከወዲሁ ካልተገባ ተግባራቸው እንዲቆጠቡም ፖሊስ አሳስቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.