Fana: At a Speed of Life!

ምሁራን፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎችም የበኩላቸውን ቢወጡ ሙስናን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሙስና እንደ ሀገር ማህበራዊ ቀውስ እየፈጠረ የመጣ በመሆኑ ቆራጥ እርምጃዎች ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የማህበራዊ ሳይኮሎጂ መምህር ዶክተር አበባው ምናየህ ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይኮሎጂ መምህር ዶክተር አበባው ምናየህ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ ሙስና ሀገር ላይ ስለሚያደርሰው ከፍተኛ ተጽዕኖና ሊወሰድበት ስለሚገባው እርምጃ አንስተዋል፡፡

ሀገራዊ ስጋት የሆነው ሙስና ከግለሰብ እስከ ቤተሰብና ማህበረሰብ ጭምር የጋራ ትግል ማድረግን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በየጊዜው መልኩን እየቀየረ የመጣው ሌብነት በዜጎች የየዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ ላይ ጭምር ጫና መፍጠሩን ቀጥሏል ያሉት ዶክተር አበባው ፥ ሂደቱ በዜጎች መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከጥቃቅን እስከ ትላልቅ ሌብነቶች ድምራቸው ማህበራዊ ቀውስ መፍጠር መሆኑን አንስተው ፥ የሀብት ማፍሪያ መንገዱ በተዘረጋ ሰንሰለት መጠቃቀምን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አለፍ ሲልም የራስን ቡድን መፍጠርና መደበቂያም ማድረግ አንዱ አካሄድ መሆኑ ሌላው የቀውስ ምንጭ ነውም ብለዋል ምሁሩ፡፡

በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በመዋቅር ምክንያት ሙስና ሊሰፋም ሊጠፋም እንደሚችል የጠቆሙት መምህሩ ፥ አሁን በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ሙስና እንዲጠፋ በተናጥልና በጋራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

በተያያዘ የህዝብ ተሳትፎ እውን እንዲሆን የመንግስት ቆራጥ እርምጃ የሚታይ ሊሆን ይገባል ያሉት ምሁሩ ፥ በዚህም የህዝብና መንግስት መተማመን ይጎለብታል ፤ ሙሰኞችም ይጋለጣሉ ፤ ተጠያቂነትም ይረጋገጣል ነው ያሉት፡፡

ምሁራን፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎችም የበኩላቸውን ቢወጡ ሙስናን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡

በኃይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.