Fana: At a Speed of Life!

በጥናት የተመሠረተ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ እያካሄድኩ ነው – የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ በተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ላይ የሚሠራው ሥራ የሕዝብን ችግር የሚፈታ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ኃይለማሪያም ከፍያለው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ÷ ዘንድሮ የሚካሄደው የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ በጥናትና ምርምር የተደገፈ እና በየትኛው ቦታ ምን መሥራት ያስፈልጋል የሚለውን በለየ መልኩ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በየትኛው አካባቢ ምን ዓይነት የአካባቢ ጥበቃ ያሥፈልጋል የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንዲሁም የደን ልማት መርሐ-ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል።

ቢሮው በአማራ ክልል ግብርና ኢኒስቲትዩት አማካኝነት ከ2006 አስከ 2015 በክልሉ የተሠሩ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች ምን ለውጥ አመጡ የሚለውን መገምገሙንም አንስተዋል፡፡

አጥጋቢ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ በተከናወነባቸው አካባቢዎች እስከ 16 በመቶ የአፈር መከላትን መቀነስ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ኃላፊው በክልል ደረጃ ያለው የአፈር መሸርሸር በ22 በመቶ መጨመሩን ያልሸሸጉ ሲሆን ፥ በዘንድሮው በጀት ዓመት ጥናት ላይ በመመሥረት የክልሉን የተፈጥሮ ሐብት ለመጠበቅ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በከድር መሀመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.