Fana: At a Speed of Life!

ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አሳጥቷል በተባለው ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከ4 ሚሊየን 515 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ አድርጓል በተባለው ሳሙኤል እጓላ ላይ ክስ መመስረቱን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ክሱ የቀረበው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ሲሆን÷ተከሳሽ ሳሙኤል እጓለ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

ተከሳሹ ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው የአሜሪካ፣ አውሮፓና ዓረብ ሀገራት የሚገኙ ግለሰቦች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ሲፈልጉ እዚያው ሀገር የሚገኙ ያልተያዙ ግብረ-አበሮቹ ገንዘቡን በመሰብሰብ የሚላክላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር፣ የባንክ ሂሳብ ቁጥር እና የገንዘቡን መጠን በሚያስተላልፉለት መረጃ መሰረት ገንዘቡን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ግለሰቦች በስሙ የከፈታቸውን የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች በመጠቀም ሲልክ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

በዚህም ባለፉት ጊዜያት ተከሳሹ 182 ሚሊየን 993 ሺህ 953 ብር ከ49 ሳንቲም ከውጭ ሀገራት ገንዘብ ለተላከላቸው ሰዎች ማስተላለፉን ነው የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላከተው፡፡

ገንዘቡ በሕጋዊ ገንዘብ አስተላላፊዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ልታገኝ የነበረውን 4 ሚሊየን 515 ሺህ 562  ከ47 ሳንቲም የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ ያደረገ በመሆኑ ግለሰቡ በፈፀመው ያለ ብሄራዊ ባንክ ፈቃድ የባንክ ሥራ መሥራት ወንጀል ተከሷል፡፡

ተከሳሹ ክሱ በችሎት ደርሶት በንባብ የተሰማ ሲሆን÷ የክሱ ማመልከቻ ላይ መቃወሚያ ካለው ለመቀበልም ለታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

ተከሳሽ ዋስትና እንዲፈቀድለት በጠበቆቹ አማካኝነት ያቀረበው ጥያቄ ላይ ዐቃቤ ሕግ ዋስትናውን በመቃወም ክርክር ያደረገ በመሆኑ ችሎቱም ተከሳሹ የዋስ መብቱ ተነፍጎ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ክሱን የመሰረተው በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ መሆኑም ተገልጿል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.