Fana: At a Speed of Life!

ማረሚያ ቤቶችን ከማረሚያ ማዕከልነታቸው ባለፈ የስልጠና እና የምርታማነት ስፍራ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ዳመነ ዳሮታ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2015 (ኤፍ. ቢ. ሲ.) ማረሚያ ቤቶችን ከማረሚያ ማዕከልነታቸው ባለፈ የስልጠና እና የምርታማነት ስፍራ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አቶ ዳመነ ዳሮታ ተናገሩ።

በወጣት ጥፋተኝነት፣ በአማራጭ ቅጣቶች እና በሌሎች የማረሚያ ቤት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መሰጠት ተጀምሯል።

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት አቶ ዳመነ፥ ከማረሚያ ቤት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ዓለም በቃኝ ከሚለው ስያሜ ጀምሮ የዕይታና የአመለካከት ችግር እንደነበር አስታውሰዋል።

በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ማረሚያ ቤቶች የትምህርት፣ የመታረሚያ እና ህብረተሠቡን የሚክሱበት ቦታ የማድረግ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር ማረሚያ ቤቶች ቀደም ሲል ከነበረበት ጥበቃ ተኮር ስራው ተላቆ ታራሚ ተኮር ወደ መሆን መቀየራቸውን ለህዝብ ለማሳየት መሰራቱን ነው ያስታወቁት።

ማረሚያ ቤቶችን የበለጠ ለማረሚያ ቤተሰቦች እና ለህብረተሰቡ ክፍት እንዲሆኑ የተጀመረው ስራ ይቀጥላል ብለዋል።

ታራሚዎች ደረጃውን በጠበቀ ማረሚያ ቤት እንዲኖሩ የማድረግ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማሻሻል ስራው በስፋት ይቀጥላልም ነው ያሉት።

የጀስቲስ ፎር ኦል ዋና ዳይሬክተር ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ፥ ኮሚሽኑ ማረሚያ ቤቶች ባለፉት አራት ዓመታት ባከናወነው ማሻሻያ ማረሚያ ቤቶችን የህዝብ ቦታ እንዲሆኑ ማስቻሉ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የኢትዮጵያ የፍትህ ዘርፍ እድገት ማሳያ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በመሆን ማረሚያ ቤቶችን ገፅታ ማሳየቱም በህዝብ ውስጥ ግንዛቤን በመፍጠሩ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው፥ ቀደም ሲል በነበረ ችግር እና በአግባቡ ተቋሙን የማስተዋወቅ ስራ ባለመሰራቱ ጥሩ ምስል እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በተቋሙ በተከናወነው የሪፎርም ስራ እና ማረሚያ ቤቶች የመታረሚያ፣ የይቅርታ እና የመገንቢያ ማዕከል እየሆኑ መምጣታቸውን የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱን ነው አቶ አድማሱ የገለፁት።

ማረሚያ ቤቶች የዕውቀት፣ የትምህርት እና የምርታማነት ማሳያ መሆናቸውን ለማሳየት ፋና ከቴሌቪዥን ስርጭቱ በተጨማሪ ወጣቱ የሚጠቀምባቸው የዲጂታል ሚዲያዎችን በመጠቀም የበለጠ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.