Fana: At a Speed of Life!

መቀሌን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አገኙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መቀሌን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
 
አገልግሎቱ በትግራይ፣ አማራና በአፋር ክልሎች በተከሰተው ጦርነት በዲስትሪቢዩሽን መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት የፀጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን ከስር ከስር መልሶ በመጠገን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸውን አካባቢዎች ዳግም ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
እስካሁንም በክልሎቹ በርካታ አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ነው የተመላከተው፡፡
 
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ እስከ ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ከአማራና አፋር ክልል በተጨማሪ በትግራይ ክልልም የቴክኒክ ባለሙያዎችን በማሰማራትና አስፈላጊ ግብዓቶችን በሟሟላት አገልግሎት የተቋረጠባቸውን አካባቢዎች ዳግም ተጠቃሚ እየተደረጉ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
 
በዚህም ከመቀሌ እና መኾኒ ሰብስቴሽን አገልግሎት የሚያገኙት መቀሌ፣ መኾኒ፣ ኩይሃ፣ ሳምረ፣ ሀገረ ሰላም፣ ጨርጨርና፣ የርብሃ አዲስ ቅኝ ቀበሌ ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያለው አገልግሎቱ፡፡
ከውቅሮ እና አዲግራት ሰብስቴሽን አገልግሎት የሚያገኙት ውቅሮ፣ ሀውዜን፣ አጽቢ፣ ፍሬወይኒ፣ አዲግራት፣ ብዘት፣ ኢንትጮና አካባቢዎቻቸው ከዛላንበሳ በስተቀር ዳግም ተጠቃሚ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
 
ከአላማጣ ሰብስቴሽን አገልግሎት የሚያገኙት አላማጣና ማይጨው ከተሞች ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መመለስ መቻሉ ተመላክቷል፡፡
 
ከሽረ ሰብስቴሽን አገልግሎት የሚያገኙ የሽረ፣ የሰለክላካና እንዳባጉና ከተሞች ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን÷ ከሽረ-አድዋ-አክሱም ያለው መስመር የጥገና ስራው በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡
 
ይህ ሲጠናቀቅም አድዋና አክሱም ከተሞች ዳግም አገልግሎቱን የሚያገኙ ይሆናል ነው የተባለው፡፡
 
ከሽረ ሰብስቴሽን አገልግሎት የሚያገኙት ሽራሮ፣ ማይሀንሳይና አዲዳእሮ ከተሞች በተዘረጋው የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በጥገና ሂደት ላይ መሆኑንም የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ከአድዋ ሰብስቴሽን አገልግሎት የሚያገኙት አድዋ፣ ራማ፣ ነበለት፣ እዳጋ አርቢ፣ እዳጋ ሀሙስ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የጥገና ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.