Fana: At a Speed of Life!

በየዘርፉ ያሉ ልሂቃን ለብሔራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በየዘርፉ ያሉ ልሂቃን በአገር ጉዳይ ላይ ተቀራርበው በመሥራት ለብሔራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር በሀገራዊ ምክክርና ዘላቂ የሰላም ግንባታ ሂደቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የክልል እና ከተማ አስተዳደር የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አመራሮች፣ የሰላም ምክክር አስተባባሪዎች እና የሲቪክ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ ለሀገራዊ ምክክሩ የመንግሥት መዋቅር ሚና ምን ሊሆን እንደሚገባ የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ሰነዱም ከመንግሥት ተቋማት ሚና ባሻገር በሀገራዊ ምክክር ላይ ስኬታማ የሆኑ እና ያልሆኑ ሀገራትን ተሞክሮ ያካተተ ነው፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ባለመፈጠሩ ምክንያት ዘላቂ ሰላምን በሚፈለገው አግባብ መገንባት አልተቻለም፡፡

ከዚህ አኳያ ሀገራዊ ምክክሩ ዜጎች በዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ እንዲሁም በታችኛው እርከን ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.