Fana: At a Speed of Life!

ተመድ የልማት መርሐግብር ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሐግብር ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ አጠቃላይ የኢትዮጵያን አሁናዊ የኢኮኖሚና ሁሉን አቀፍ የልማት ስኬቶችና ተግዳሮቶች አብራርተዋል።

በዚህም መንግሥት የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እና በኢንቨስትመንት፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በግብርናና ሌሎች የልማት መስክ ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል።

በፈረንጆቹ 2019 ተግባራዊ መሆን የጀመረው አካታች ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተግባራዊ የሆነ እምርታዊ ለወጦችን እያስመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።

በትምህርት፣ በጤና፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ሀገሪቷ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገቧንም ነው ያነሱት።

ሂደቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ችግር፣ የኮቪድ 19 ተጽእኖ ሥር የቆየ ቢሆንም በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ጠንካራ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄም ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይም ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የእድገት አቅጣጫ በማስቀጠል ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት ትሰራለች ነው ያሉት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሐግብር የኢትዮጵያ ተወካይ ቱሩሃን ሳልህ÷ በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ የኢኮኖሚና ሁሉን አቀፍ ሪፎርሞች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የተባበሩት መግሥታት ድርጅት የልማት መርሐግብር ሪፎርሙን በመደገፍ የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.