Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፈን መንግሥት ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፈን መንግሥት ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

አቶ አሻድሊ ቀደም ብሎ በክልሉ የሰላም እጦት መከሳቱን አስታውሰው÷ ሰላም እንዲመጣ በየደረጃው ያለው አመራር ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ለክልሉ ፀጥታ መደፍረስ ዋና ምክንያት በክልሉ የነበረው የፖለቲካ ስሪት መሆኑን እና የሌሎች አካላት ሚና አባባሽ እንጂ ዋና ምክንያት አለመሆኑን አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።

በክልሉ የነበሩትን የፖለቲካ ስሪት ችግሮች መፍታት በመጀመሩ ዘላቂ ሰላም እየመጣ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በኅብረ ብሔራዊ የመደመር እሳቤ የክልሉን ሰላም የማስፈን ተግባር ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑ ታውቆ÷ ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል አቶ አሻድሊ፡፡

የክልሉን ሰላም መሆን የማይፈልጉ አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት የክልሉን ገጽታ ለማጠልሸት እና ለማፍረስ ቢሞክሩም÷ የሚፈርስ ሀገርና ክልል ያለመኖሩን በማረጋገጥ ከድርጊታቸው እየታቀቡ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡

ከክልሉ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራርመው ወደ ክልሉ የገቡ የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን) አባላት የተሃድሶ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን እና የሰላም ስምምነቱ ለሀገራዊ፣ ክልላዊና ቀጣናዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴና ልማት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።

በመተከልና በካማሺ ዞኖች እየመጣ ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ከተፎካካሪ የፖለታካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረውን ተቀራርቦ በጋራ የመስራት ባህል ለማዳበር መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.