Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የዳቦ ምርት ፍላጎትን ለመመለስ በሁሉም ክፍለከተማ በአማካይ 2 የዳቦ ፋብሪካ እንዲኖር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የዳቦ ምርት ፍላጎት መጨመር መሰረት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በአማካይ ሁለት የዳቦ ፋብሪካዎች እንዲኖሩ ታስቦ እየተሠራ መሆኑን የአስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ መስፍን አሰፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ አስተዳደሩ በየዓመቱ በአማካይ ለሸገር ዳቦ ፋብሪካ እስከ 800 ሚሊየን ብር በመደጎሙ ለሸማቹ አንድ ዳቦ በ2 ብር ከ10 ሣንቲም እየቀረበ ነው፡፡

ከሸገር ዳቦ ፋብሪካ እና በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ከተገነቡት የዳቦ ፋሪካዎች በተጨማሪ÷ የዳቦ ምርት ፍላጎትን ለመመለስ በልዩ ሁኔታ ለባለሀብቱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ከ22 በላይ የዳቦ ፋብሪካዎች እንዲኖሩ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የንግድ እንቅስቃሴውን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ያሉት አቶ መስፍን÷ በተለይም የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የገቢ መሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ከ800 በላይ መዳረሻ ሱቆች ያሏቸው 148 ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መኖራቸውን እና የምርት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ለማኅበራቱ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ብድር ተመቻችቶ የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ከግብይት ሰንሰለት ጋር ያለውን ችግር ለመቅረፍም÷ ሸማች ማኅበራት በቀጥታ ከአርሶ አደሩ እንዲሸምቱ፣ አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ የሚያቀርቡበት የእሁድ ገበያ ማመቻቸት እንዲሁም በየዘርፉ የገበያ ማዕከላት መገንባቱንና በግንባታ ላይ ያሉ መኖራቸውን ነው የገለጹት፡፡

በእሁድ ገበያ ያለው የምርት አቅርቦት በሚፈለገው ልክ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከተቆረቆረች ጀምሮ እስካለፉት አራት ዓመታት ድረስ ሁለት (ቄራ እና ሸጎሌ) የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላት ብቻ እንደነበሩ አስታውሰው÷ የአትክልትና ፍራፍሬ እና የሰብል ገበያ ማዕከላት ጭራሽ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል፡፡

በአራት ዓመታት ውስጥ አራት (ኮልፌ፣ አቃቂ፣ የካ ካራሎ እና ለሚኩራ) የቁም እንስሳት፣ ሁለት (ላፍቶ እና ጀሞ) የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም አንድ (አቃቂ) የሰብል ገበያ ማዕከላት መገንባታቸውንም አብራርተዋል።

በዚህም ከተማዋ ከተቆረቆረች ጀምሮ የነበሩትን ሁለት የግብይት ማዕከላት ወደ ሰባት ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፥ እነዚህ ማዕከላት ምርትን ለሸማቹ በቅርበት በማቅረብ እና የገበያ ሰንሰለትን በማሳጠር ረገድ ጥቅማቸው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠናቀቁ ሦስት የግብይት ማዕከላት መኖራቸውን ያመላከቱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ÷ ይህም ሆኖ ካለው የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር አኳያ በቂ ነው ተብሎ ስለማይታመን በቀጣይ የማስፋት ሥራ በትኩረት እንደሚሠራም ነው ያስረዱት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.