Fana: At a Speed of Life!

የኬንያ ልዑክ የደጎዲያ ጎሳ ባህላዊ መሪ የክብር ሽልማት ለመስጠት ጅግጅጋ ከተማ ገባ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬንያ ልዑክ የሰላም አባት ለሆኑት የደጎዲያ ጎሳ ባህላዊ መሪ የክብር ሽልማት ለመስጠት ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ  ከተማ ገብቷል፡፡

ልዑኩ ከቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የተበረከተውን የሰላም ሜዳሊያ ሽልማት ለማበርከት ነው ጅግጅጋ ከተማ የገባው።

የልዑካን ቡድኑ አባላት ጅግጅጋ ገራድ ዊልዋል አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ልዑኩ በቆይታው በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ክብር ከሚሰጣቸው ባህላዊ የጎሳ መሪዎች መካከል አንዱ ለሆኑት የደጎዲያ ጎሳ መሪ ወበር አብዱላሂ ወበር አብዲ የሰላም አባትነት የእውቅና እና የሜዳሊያ ሽልማት ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል።

ወበር አብዱላሂ ወበር አብዲ በሶማሌ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በማርገብ ዜጎች ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ ላበረከቱት አስተዋፅኦ  በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የሊበን አካባቢ የዲጎዲያ ጎሳ ባህላዊ መሪ የሆኑት ወበር አብዱላሂ ወበር አብዲ በግጭቶች ምክንያት በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ቤትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከተለያዩ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር በጋራ የሚሰሩ የሰላም አባት መሆናቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.