Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የቪዛ ስርዓቷን ለአፍሪካዊያን የበለጠ በማቅለል እመርታ ማሳየቷን የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት አመለከተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ማለትም ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2022 ለአፍሪካዊያን የቪዛ ስርዓቷን በማቅለል በሯን ይበልጥ ክፍት በማድረግ እመርታ ማሳየቷን የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት አመለከተ።

በአፍሪካ ጥቂት አገሮች በ2016 እና 2022 መካከል የቪዛ ስርአታቸውን በማቅለል ጎልተው መታየታቸውንም ባንኩ በሪፖርቱ ጠቅሷል።

እንደ ሪፖርቱ፥ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሌላ የአፍሪካ ሀገር ዜጋ ቪዛን መዳረሻ ላይ እንዲያገኝ በማድረግ አሊያም የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አማራጮችን ማቅረብ መጀመራቸውን ሪፖርቱ አያይዞ ገልጿል፡፡

ከምስራቅ አፍሪካ በተሻለ የቪዛ ሥርዓትን በማቅለል ረገድ ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ብቻ ጠቅሷል።

በዚህም ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ እመርታን ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ለአፍሪካዊያን ጎብኚዎች በራቸውን በተሻለ ክፍት ካደረጉ 20 አገራት መካከል 17ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመላክቷል፡፡

ይህም የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ በፈረንጆቹ 2021 ያጣችውን ደረጃ መልሳ እንድታገኝ እንዳስቻላት ነው የተጠቀሰው፡፡

ከ2016 እስከ 2022 ከአህጉሪቱ የተሻለ የቪዛ ሥርዓታቸውን ለጎብኚዎች በማቅለል ቀዳሚ የሆኑ አራት ሀገራት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ማለትም ቤኒን፣ ጋና፣ ናይጄሪያ እና ጋምቢያ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የአገራቱ የቪዛ ሥርዓትን ማሻሻል እና ማቅለል በአህጉሪቱ የንግድ ግንኙነትን እና የጉብኝት እንቅስቃሴ እንዲያድግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.