Fana: At a Speed of Life!

ወደ ትግራይ ክልል 229 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶች መሰራጨታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሠላም ሥምምነቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል 229 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁሶች መሰራጨታቸውን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለጸ።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንዳሉት÷ የሰላም ሥምምነቱን ተከትሎ በሦስት አቅጣጫዎች መድሃኒቶች ወደ ትግራይ እየተሰራጩ ነው።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር 229 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የህክምና ግብዓቶች ወደ ትግራይ ክልል መላካቸውን ጠቁመው በመቀሌ እንዲሁም በሽረ የሚገኙ የአገልግሎቱ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በከፊል ሥራ መጀመራቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የመድሃኒቶቹ ዓይነትም የጤና ፕሮግራም መድሃኒቶች (የኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የወባ እንዲሁም የእናቶችና ህጻናት መድሃኒቶች) መሆናቸውን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለመደበኛ፣ ለሕይወት አድን የሚውሉ መሰረታዊ መድሃኒቶች፣ ለህክምና አገልግሎትና ለላቦራቶሪ ግብዓት የሚውሉ ኬሚካሎች መሰራጨታቸውንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

እንደ ስኳርና ደም ግፊት የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግሉ መድሃኒቶች መካተታቸውንም ገልፀው ሁለተኛ ዙር የመድሃኒት ሥርጭትም በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.