Fana: At a Speed of Life!

ከ141 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጉምሩክ ኮሚሽን ከኅዳር 30 እስከ ታኅሥሥ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከ141 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል 81 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና 60 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የወጪ ኮንትባንድ ዕቃዎችን ነው በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽኅፈት ቤቶች በተሰሩ ሥራዎች የያዘው፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሐኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ ኮምቦልቻ እና አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ ጽኅፈት ቤቶች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ መሆናቸውንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 10 ግለሰቦች እና 11 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.