Fana: At a Speed of Life!

የመቀሌ ሕዝብ ደኅንነት ሊጠበቅ ይገባዋል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመቀሌ ሕዝብ ደኅንነት ሊጠበቅ ይገባዋል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

መንግስት ኮሙኒኬሽን የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፡-

የመቀሌ ሕዝብ ደኅንነት ሊጠበቅ ይገባዋል

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝብ እና ለሀገር ሰላም ሲባል በሰላም ስምምነቱ የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድርና ሳያንጠባጥብ በመፈጸም ላይ ይገኛል።

ይህን የሽግግር ወቅት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በአንዳንድ የመከላከያ ኃይላችን ባልደረሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች ኅብረተሰቡን ሰላም የሚነሡ የተደራጁ ዘረፋዎች እየተካሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተለይም በመቀሌ ከተማ በመንግስትና በንግድ ተቋማት ላይ በፓትሮል የታገዘ ከፍተኛ ዝርፊያ መኖሩን መረጃዎች እየጠቆሙ ነው። ሕዝቡም በከፍተኛ ምሬት ላይ መሆኑን በስልክና በሌሎችም መንገዶች እያሳወቀ ይገኛል። በሰላም ስምምነቱ ምክንያት ከግጭት የሚያተርፉት ትርፍ የቀረባቸው አካላት ይሄንን እንደሚያደርጉ አያጠራጥርም። ይህን ወንጀል የሚፈጽሙ ሁሉ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ሊገነዘቡ ይገባል።

መንግሥት በአካባቢው የሚገኙና የሕዝብ ደኅንነት የሚገዳቸው አካላት ከሕዝቡ ጎን ቆመው ወንጀለኞችን እንዲታገሉ ጥሪ እያደረገ የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ያለበትን ኃላፊነት ለመፈጸም አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጥ ይወዳል።
ታኅሣሥ 8/2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.