Fana: At a Speed of Life!

በእንጨት ሳጥን የጦር መሳሪያ ደብቆ ሲያዘዋውር የተገኘ ተጠርጣሪ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በእንጨት ሳጥን የጦር መሳሪያ ደብቆ ሲያዘዋውር የተገኘ ተጠርጣሪ እጅ ከፍንጅ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ዛሬ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ ትልቁ የሃገር አቋራጭ መናኸሪያ ውስጥ ከጠዋቱ 1ሰዓት ላይ ነው ተብሏል።

ተጠርጣሪው በህገ-ወጥ መንገድ በማይጠረጠር ሁኔታ ለዚሁ ህገ ወጥ ተግባር ማስፈፀሚያ ባዘጋጀው ከእንጨት በተሰራ ሳጥን ውስጥ በጨርቅ ጠቅልሎ የጦር መሳሪያዎችን ደብቆ ይዞ እንደነበርም ነው የተነሳው፡፡

በዚህም 1ምንሽር ፣ 1 አብራራው ጠመንጃ እና 1 ቱርክ ሰራሽ ኢኮልፒ ሽጉጥ ጭኖ ወደ ጎጃም ሊሄድ ሲል በመናኸሪያው ውስጥ በጫኝና አውራጅ በተደረጁ አጋዥ ኃይሎች እጅ ከፍንጅ መያዙን ፖሊስ አስታውቋል።

ግለሰቡ የጦር መሳሪያዎቹን ከደቡብ ኢትዮጵያ ይዞ ማምጣቱን ለፖሊስ ቃሉን መስጠቱን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር እየተሰሩ ባሉ ስራዎች የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ስለሆነ ይሄው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን ያስተላለፈው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.