Fana: At a Speed of Life!

በዛምቢያ 27 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል በሚል የተሰራጨውን ዘገባ የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው ተላከ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛምቢያ መዲና ሉሳካ አቅራቢያ ኢትዮጵያውን ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 27 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ሁኔታውን የሚመረምር ቡድን ወደ ስፍራው ልኳል፡፡
ሚኒስቴሩ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በሚደረግ ህገወጥ ጉዞ ኢትዮጵያን ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 30 ሰዎች በሰሜናዊ ማላዊ በጅምላ ተቀብረው መገኘታቸውን የማላዊ መንግስት ከሳምንታት በፊት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጣሪ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን አስታውሷል።
ቡድኑ ከታህሳስ 2 ቀን እስከ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በማላዊ በነበረው ቆይታ ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከማላዊ ፖሊስ አገልግሎት፣ ከማላዊ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዲፓርትመንት ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል ።
የውጭ ጉዳይ አጣሪ ቡድን ከማላዊ መንግሥት ኃላፊዎች ጋር በጅምላ የተቀበሩት ሰዎች ምርመራ ሂደት ያለበት ደረጃ ፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ተጠያቂ በሚሆኑበት ጉዳይ ውይይት አካሂዷል ነው የተባለው፡፡
እንዲሁም በእስር ላይ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዝርዝር መረጃ ማግኘት በሚቻልበት እና ከእስር ተፈተው ወደ አገራቸው መመለስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያደረጉት ውይይት ውጤታማ ሆኖ መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡
በውይይቱም÷ በመላው ማላዊ በእስር ላይ የሚገኙ 245 ኢትዮጵያውያን ሁሉም በይቅርታ ተፈተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ስምምነት ላይ ተደርሷል፤እስረኞቹን የሚመለከት መረጃ ለልዑካን ቡድኑ እንደተሰጠ ተገልጿል።
በቀጣይም እስረኞቹን ወደ አገር ቤት የመመለሱን ስራ ከማላዊ የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱም ታውቋል።
ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብለው ከተጠረጠሩት እና በጅምላ ተቀብረው የተገኙ ሟቾችን በሚመለከት ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የማላዊ መንግስት እስካሁን ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ጉዳያቸው በአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑም ተመላክቷል።
ቀሪ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በመያዝ ለህግ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያተደረገ እንደሚገኝና ቡድኑ በማላዊ ቆይታው ሟቾች የተቀበሩባቸውን የመቃብር ስፍራዎች ጭምር መጎብኘቱ ታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጣሪ ቡድን በማላዊ የነበረውን ቆይታ በማጠናቀቅ ወደ ዛምቢያ ማምራቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ቡድኑ በዛምቢያም ባለፈው ሳምንት ከመዲናዋ ሉሳካ ወጣ ባለ ስፍራ ኢትዮጵያውን ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 27 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ሁኔታውን የሚመረምር ይሆናል ነው የተባለው።
የህገወጥ የሰዎች ዝውውር አሳሳቢ በመሆኑና ችግሩን ለመከላከል የሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.