Fana: At a Speed of Life!

ሰሜን ኮሪያ ሁለት ባላስቲክ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ በዛሬው ዕለት ሁለት የባላስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ጃፓን ባህር ማስወንጨፏ ተሰምቷል፡፡

ፒዮንግያንግ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ያስወነጨፈችው ጃፓን የመከላከያ አቅሟን ለማጠናከር የሚያስችል የ320 ቢሊየን ዶላር በጀት ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ ሁለቱ የሰሜን ኮሪያ ባላስቲክ ሚሳኤሎች 500 ኪሎ ሜትር ተምዘግዝገው ከጃፓን ብቸኛ የኢኮኖሚ ዞን ውጭ መውደቃቸውን አስታውቋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ የጥምረት ባለስልጣናት በበኩላቸው÷ ከሰሜን ኮሪያ ሰሜን ፒዮንግያንግ ግዛት የተወነጨፉ ሁለት ሚሳኤሎች እንደተመለከቱ መናገራቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ባለስልጣናቱ ወታደሮቻቸው ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ጥቃቱን ለማክሸፍ ዝግጁ እንደሆኑ እና ሁኔታውን በቅርበት እንደሚከታተሉ ጠቁመዋል፡፡

ፒዮንግያንግ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዳ ከፍተኛ ግፊት ያለው የነዳጅ ሞተር በሳለፍነው ዓረብ ዕለት በተሳካ ሁኔታ መሞከሯም ተገልጿል፡፡

ሰሜን ኮሪያ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 62 የባላስቲክ ሚሳኤሎች እና 3 የክሩዝ ሚሳኤሎች ማስወንጨፏን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.