Fana: At a Speed of Life!

የረጲ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጥገና እየተደረገለት ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የቆሻሻ ማጣሪያ፣ የስቲም ተርባይንና ጀነሬተር ጥገና እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ኤባ እንዳሉት ፥ ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ እየተከናወነ ያለውን ጥገና እስከ ታህሳስ መጨረሻ በማጠናቀቅ ጣቢያውን ኃይል ወደ ማምረት ለመመለስ እየተሠራ ነው፡፡

ወደ ኃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚመጣው የቆሻሻ ጥራት ከሚጠበቀው ደረጃ በታች መሆኑ፣ ማመንጫ ጣቢያው በባህሪው የተለየ በመሆኑና የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት በመኖሩ ብልሽት እንደሚያጋጥም ገልፀዋል፡፡

ጣቢያው ለጊዜው ኃይል ማምረት ቢያቋርጥም በአሁኑ ወቅት በቀን በአማካይ 600 ቶን ቆሻሻ በማቃጠል ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

ጣቢያው ኃይል ወደ ማምረት ሲመለስ ቆሻሻ የመቀበልና የማቃጠል አቅሙን በመጨመር ለአካባቢ ጥበቃና ለዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

የጥገና ሥራው በራስ አቅም እየተከናወነ መሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለጣቢያው የጥገና ሥራ የሚያገለግሉ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለማቅረብ ተቋሙ ቻይና ናሽናል ኤሌክትሪክ ኢንጂነሪንግ ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር ወደ ሥራ መገባቱም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.