Fana: At a Speed of Life!

መከላከያ በሚገኝባቸው የትግራይ አካባቢዎች ሆስፒታሎችን መልሶ በማደራጀት አስፈላጊው የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ነው – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ በሚገኝባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች ባሉ ሆስፒታሎች እና ጤና ተቋማትን መልሶ በማደራጀት አስፈላጊው አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
 
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር ኮሚቴ ተዋቅሮ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
 
በዚህ መሰረትም በመጀመሪያ ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው በመላክ የጤና ተቋማቱ ያሉበት ሁኔታን የመገምገም ስራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
 
በቀጣይም በተቋማቱ የተገኙ ሃብቶች ባሉበት እንዲደራጁ እና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተሟልተው ባሉበት ደረጃ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡
 
በተለይም በሽረ ኮሪደር እና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎች እና ጤና ተቋማት 2 ሺህ 500 በላይ ነባር ሰራተኛችን ወደ ስራ በማስገባት አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን አንስተዋል፡፡
 
በሽረ ኮሪደር ብቻ አክሱም ፣ ሽራሮ፣ ሽረ፣ ዓድዋ፣ ደሃሮ፣ እንዳባጉና፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ሰለኽላኻ ጨምሮ 8 ሆስፒታሎች እንዲሁም 14 ጤና ጣቢያዎች ስራ ጀምረው አስፈላጊውን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ተቋማቱ በድንገተኛ እና በተመላላሽ ታማሚዎች አገልግሎት መጀመራቸውን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ አሁን ላይ የመብራት፣ ስልክ እና ሌሎች አገልግሎቶች መጀመር ስራውን ይበልጥ እንዳቀላጠፈው ተናግረዋል፡፡
 
የመድሃኒት አቅርቦትን በተመለከተም በሽረ የሚገኘው የመድሃኒት አቅርቦት ቅርንጫፍ በአስቸኳይ ስራ እንዲጀምር መደረጉን እና ለዚህም ከጎንደር እና ደሴ ቅርንጫፍ አስፈላጊው የመድኃኒት ግብዓት እየተላከ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
በዚህ መሰረትም ከጎንደር እና ደሴ አቅርቦት 35 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶች እና የህክምና ግብዓቶች ወደ ሽረ ኮሪደር እና ሌሎች አካባቢች እየተሰራጩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
 
በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ በዓለም ጤና ድርጅት በኩል 78 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የስኳር፣ ወባ፣ ኩላሊት፣ ቲቢ፣ ለስነ ተዋልዶ እና ቋሚ የጤና ችግር ላለባቸው ህሙማን የሚያገለግሉ የሕክምና ግብዓቶችን ወደ መቀሌ መላኩን ጠቁመዋል፡፡
 
በተጨማሪም በአጋር ድርጅቶች በኩል158 ሜትሪክ ቶን በላይ መድሃኒቶች እና አስፈላጊ የተባሉ የሕክምና ግብዓቶች ወደ መቀሌ መጓጓዛቸውን ነው የገለጹት፡፡
 
ከመብራት መጀመር ጋር ተያይዞም የመድሃኒት የቅዝቃዜ ሰንለሰለቱ እንዲሰራ በማድረግ የክትባት እና ሌሎች አገልግሎቶችን በሰፊው የማሰራጨት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
 
በቀጣይም በአካባቢው የሚስተዋለውን የአምቡላንስ ችግር በመቅረፍ አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት በሙሉ አቅም ተደራሽ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.