Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የተወሰኑ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንድታስገባ የተሰጣት ዕድል ምን ትሩፋት ይዞ መጣ?

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት ዘርፈ ብዙ ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ እና እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ቤጂንግ በ “ቤልት ኤንድ ሮድ” የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ሠንሠለት ውስጥ በርከት ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡

ለአብነትም፥ የሳይኖ ኢትዮጵያ የንግድ ልውውጥ ሲቃኝ በፈረንጆቹ ከ2015 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ ቻይና ለኢትዮጵያ ምርት አንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መዳረሻ ናት።

ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ከምትልካቸው ምርቶች መካከል አብዛኛዎቹ የግብርና ውጤቶች መሆናቸውን እና ያንን ተከትሎ ቻይናም የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ እንዲልኩ ካለፈው ዓመት ጀምሮ መፍቀዷ የሁለቱ ወገኖች የንግድ ልውውጥ ማደግን እና ወደፊት ለማራመድ ፍላጎት መኖሩን ማሳያ መሆኑን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር ሙሴ ምንዳዬ ሰሞኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሰሞኑን የቻይና መንግሥት 10 ሀገራት የተወሰኑ የምርት ዓይነቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና ገበያ እንዲያስገቡ ፈቃድ መስጠቱ ሌላኛው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ዕድሉ የተሰጣቸው ሀገራትም ከአፍሪካ÷ ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒቢሳው፣ ሌሴቶ፣ ማላዊ፣ ሳኦቶሜ- ፕሪንሲፔ ፣ ታንዛኒያ ፣ኡጋንዳ እና ዛንቢያ ሲሆኑ÷ ከኤዥያ ደግሞ አፍጋኒስታን ናቸው፡፡

ከእዚሁ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ ከ2003 ጀምሮ የተወሰኑ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና በመላክ ላይ እንደምትገኝ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈው ሣምንት ደግሞ በነበራት ላይ 1 ሺህ 644 የምርት ዓይቶችን ያለቀረጥ ወደ ቻይና ገበያ ምርቶቿን እንድትልክ ዕድል ተሰጥቷል፡፡

ቻይና የትኞቹ ምርቶች ወደ ግዛቷ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ፈቀደች?

በንግድና ቀጣዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ቁምነገር እውነቱ፥ ኢትዮጵያ 1 ሺህ 644 የምርት ዓይነቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ግዛቷ እንድታስገባ ቻይና ፈቃድ መስጠቷን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

የምርቶቹ ዓይነት በቁጥር በርከት ማለቱን እና የግብርና እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

ቻይና ፈቃዱን ለኢትዮጵያ ያሳወቀችው ታኅሣሥ 3 ቀን 2015 ዓ.ም.መሆኑን እና የምርቶቹ የክብደት መጠን፣ የሚላኩበት ጊዜ እንዲሁም እስከ መቼ ድረስ የሚቆይ ዕድል ነው የሚለው አለመገለጹን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ዕድል የምታገኘው ትሩፋት ምንድን ነው?

በምርቶቹ ልየታ፣ ዝግጅት እና አላላክ ላይ እንደሀገር መንግሥት የሚያስቀምጠው አቅጣጫ እንደሚኖር ይጠበቃል ያሉት ወይዘሮ ቁምነገር፥ ከዚህ ዕድል ኢትዮጵያ በሙሉ አቅሟ እያመረተች የምትልካቸው ምርቶች ላይ የበለጠ ተጠቃሚ እንደምትሆን አመላክተዋል፡፡

ፈቃድ ያገኙ እና ወደ ቻይና ገበያ የሚላኩ ምርቶችን በዓይነትና በመጠን ለመለየት ሥራ መጀመሩን ጠቁመው፥ ለአብነትም ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወጪ ንግድ (በኤክስፖርት ምርት) ለሚከታተላቸው 15 ዋናዋና ተቋማት ዕድሉ ከተሰጠን ዝርዝር ውስጥ የሚያመርቷቸውን ምርቶች እንዲያሳውቁ የተላከልንን ዝርዝር አያይዘን ደብዳቤ ልከናል ይላሉ፡፡

እነዚህ 15 ተቋማት ደግሞ በሥራቸው ለሚገኙ ማኅበራት እና ተቋማት እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

በዚሁ መሠረት÷ ለኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና አልባሳትላኪዎች ማኅበር፣ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለማዕድን ሚኒስቴር፣ ለቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ ለኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ለኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር፣ ለውመን ኢን ኮፊ፣ ለኢትዮጵያ ቆዳ ላኪዎች ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ ሥጋ አምራቾች እና ላኪዎች ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ላኪዎች ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ ቅመማቅመምአመልማላማና መዓዛማ ቅጠላቅጠል አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር እንዲሁም ለኢትዮጵያ ማርና ሰም አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ቀጣይ ያለውን ሥራ ለመሥራት እንዲመቻቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደብዳቤ መጻፉን አብራርተዋል፡፡

ምርቶቹ መቼና እንዴት ይላካሉ? የሚለው ጊዜ ስለሚፈልግ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ የምርቶቹ ዓይነት እንዲሁም መጠን ሲታወቅ በሂደት እንደሚመለስ አመላክተዋል፡፡

ከቀረጥ ነጻ ዕድል መገኘቱ ገቢን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ስላለው፥ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ብቻ የሚሠራ አለመሆኑንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ስለሚፈልግ ሥራው በቅንጅት ይከናወናል ነው ያሉት፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች የኢኮኖሚክስና ልማት መምህር፣ አማካሪ እንዲሁም የንግድና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተንታኝ ዶክተር ንጉሤ ስሜ፥ ቻይና ለኢትዮጵያ የሰጠችው ዕድል የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ከማሳደግ በተጨማሪ የተቀዛቀዘውን የአጎዋ አንቅስቃሴ ለማካካስ እንደሚያግዝ ይናገራሉ፡፡

ምርቶቹ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንዲገቡ ዕድል መገኘቱ በቻይና ገበያ ውስጥ ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ረገድ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚያስችልም ነው የገለጹት፡፡

ዕድሉ አንድም ለሀገር ገጽታ እና ዕድገት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለአምራቹ፣ ለባለሀብቱ እና ለንግዱ ዘርፍ እንቅስቃሴ አበረታች ስጦታ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ቀደም ሲል ለውጪ ገበያ ሲቀርቡ የነበሩት ምርቶች በአብዛኛው ውስንና ተጨማሪ ዕሴት ያልተጨመረባቸው (ጥሬ ዕቃዎች ) እንደነበሩ አስታውሰው፥ በዚህ ዕድል ግን ያለቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንዲላኩ የተፈቀዱት በቁጥር በርካታ ያለቀላቸው ምርቶች መካተታቸው ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡ ይህም በቻይና ገበያ የኢትዮጵያ ምርቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ዶክተር ንጉሤ፥ ዕድሉ በሁለቱ ሀገራት ያሉትን አምራቾችና ሸማቾች በማገናኘት እና ምርቶቹ የሚገቡት ከቀረጥ ነጻ በመሆኑ ቻይናውያን ሸማቾች በርካሽ እንዲሸምቱ ያስችላልም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የቀረጡ መቅረት በሌላ አገላለጽ ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገ ይቆጠራል፤ ምክንያቱም ለቀረጥ መከፈል የነበረበት ገንዘብ በቀጥታ ለሀገር ገቢ ይሆናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እና የሀገራቱን ወዳጅነት በተለያየ ዘርፍ የበለጠ እንደሚያሳድገውም ያምናሉ።

የዚህ ዕድል ክፍተት እና የተሻለው ዕድል የቱ ነው?

እንደ ወይዘሮ ቁምነገር ገለጻ ከሆነ፥ ኢትዮጵያ 1 ሺህ 644 የምርት ዓይነቶችን ወደ ቻይና ከቀረጥ ነጻ እንድታስገባ ፈቃድ ብታገኝም ሁሉም የምርት ዓይነቶች ይላካሉ ማለት ግን አይደለም፡፡ ለዚህም ሁሉም የምርት ዓይነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመረቱ አለመቻላቸውን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

ከዚህ ሐሳብ እንደምንረዳው እንደዚህ ዓይነት ዕድሎች በጅምላ ለተመረጡ ሀገራት ተመሳሳይ ምርቶች እንዲልኩ ከመጠየቅ ይልቅ እያንዳንዱ ሀገራት የሚያመርቱትን እና ያላቸውን ጥሬ ዕቃ ታሳቢ አድርጎ ዕንድሉ ቢሰጥ የበለጠ ሀገራቱን መጥቀም እና ማገዝ ያስችላል፡፡

አሁን በተሰጠው ዕድል መሠረት ኢትዮጵያ የተሰጣትን ኮታ (1 ሺህ 644 የምርት ዓይነቶች) ሙሉ በሙሉ መላክ ካልቻለች እና “ተሰጥቶሻል” በተባለችው ዕድል ልክ መጠቀም ካልቻለች ትርፉ ምኑ ላይ ነው?

ስለሆነም አንድም ከዕድል ሰጭው አካል በሌላ በኩል ደግሞ ከዕድሉ ተቀባይ ሀገራት አንጻር ሊታሰብባቸው የሚገባቸው መሠረታዊ አካሄዶች መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡

ለቀጣይ ማን ምን ይሥራ?

በመንግሥት በኩል÷ ጉዳዩ የሚመለከታቸው እና ምርታቸውን እንዲያሳውቁ የተጠየቁ ተቋማት ያላቸውን የምርት ዓይነትና መጠን ሲያሳውቁ ምርቶቹ አስገዳጁን የጥራት ደረጃ ስለመጠበቃቸው፣ በአላላኩ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መንግሥት በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ወይዘሮ ቁምነገር አረጋግጠዋል፡፡

እንደ ዶክተር ንጉሤ ስሜ ዐተያይ ከሆነ ደግሞ፥ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንዲላኩ የተፈቀዱት ምርቶች ዓይነት በርካታ እንደመሆኑ ይህን ዕድል መጠቀም የኢትዮጵያ ድርሻ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ባለሀብቱ በደንብ መበረታታት አለበት፤ አምራቹ መጠንከር አለበት፤ መንግሥትም ከፖሊሲ አንጻር እንዴት አድርገን መጠቀም እንችላለን የሚለውን ሊያስብበት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

አሜሪካ የአፍሪካ ሀገራት ከኮታ እና ቀረጥ ነፃ ምርታቸውን ወደ ሀገሪቱ እንዲያስገቡ የሰጠችው የአጎዋን ዕድል እንዲመለስ መበርታት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በአምራቹ በኩል÷ አምራቹ እንደዚህ ዓይነት ዕድሎች ሲገኙ ተጠቃሚነቱ ከፍ እንዲል የሚያመርታቸውን የምርት ዓይነቶች በስብጥር አብዝቶ ማምረት እና መጠንከር ይጠበቅበታል፡፡

ማምረት ብቻውን በቂ ወይም ስኬት አለመሆኑን በመገንዘብም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ጥራትን ያስቀደመ አሠራርን ሊከተል ይገባል፡፡

በመጨረሻም ዶክተር ንጉሤ ስሜ የኢትዮጵያና ቻይናን የንግድ ግንኙነት በተመለከተ በ2020 የወጣ መረጃን ዋቢ አድርገው ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ ያለፉት 25 ዓመታትን በማሳያነት ወስደን ብንመለከት ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልከው በየዓመቱ በአማካይ ከ23 ነጥብ 7 እስከ 24 በመቶ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ደግሞ 19 በመቶ ገደማ እድገት አለው፡፡

ይህም ወደ ቻይና የሚላከውን ምርት ዕድገት እና የቻይና እና የኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት እንደሚያሳይ ገልጸው÷ በሀገር ውስጥ የሚገኙ አምራቾች፣ ባለሀብቶች እና መንግሥት የዛሬውን ጨምሮ ወደፊት የሚኖረውን ተስፋ በመገንዘብ ዘርፉ ላይ በልዩ ትኩረት እንዲሠሩ ይመክራሉ፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.