Fana: At a Speed of Life!

የ12 ዓመቷን ታዳጊ ገድለው በድብቅ ሊቀብሩ ነበር የተባሉ ቀጣሪዎች በ25 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12 ዓመት ታዳጊ የቤት ሰራተኛቸውን ገድለው በድብቅ ሊቀብሩ ሲሉ ተይዘዋል የተባሉ ግለሰቦች በ25 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ምርመራውን በመምራት ክስ መስርቶ ክርክር በማድረግ አጥፊዎቹ እንዲቀጡ አድርጓል ተብሏል።

ክርክሩን የመራው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

አንደኛ ልጃለም ጌታቸው ታዬ እና ሁለተኛ ቆንጂት ሙለታ በቀለ የተባሉ ባልና ሚስት ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ማንጎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከታህሳስ 17 እስከ ጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ሟች አስቴር ነገሰን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ከገደሏት በኋላ የሟችን አስከሬን በድብቅ ለመቅበር  ሲሞክሩ እንደተያዙ የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

ግለሰቦቹ ከተያዙ በኋላ ምርመራ ሲካሄድ በሟች ላይ ባደረሱት ጉዳት ምክንያት ህይወቷ ማለፉ በማስረጃ በመረጋገጡ ዐቃቤ  ሕግ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ መስርቶ ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ተከሳሾችም በችሎት ቀርበው ክሱ ተነቦላቸው ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም ብለው ሲከራከሩ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ አስደግፎ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ያረጋገጠ በመሆኑ እና ተከሳሾችም ይህን የዐቃቤ ሕግ ክስ እና የቀረበባቸውን ማስረጃ እንዲያስተባብሉ በተሰጠ ብይን መሰረት ሁለት የመከላከያ ምስክር አቅርበው አሰምተዋል፡፡

የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበሉ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ በቀረበባቸው ክስ እና ማስረጃ መሰረት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ሰጥቶ ቅጣት ለመወሰን ለዛሬ ቀጠሮ መስጠቱ ተጠቅሷል፡፡

ተከሳሾችን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል በሚል እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ እና ተከሳሾች ለ5 ዓመት መብቶቻቸው እንዲሻሩ ተወስኖባቸዋል፡፡

በአቅራቢያ በሚገኙ ከፍትሕ ጎን በሚቆሙ ሰዎች አማካኝነት አጥፊዎች ተቀጥተው ፍትሕ እንዲሰፍን ሰራተኞችም ሲበደሉ ህብረተሰቡ አይቶ ማለፍ እንደሌለበት ፍትህ ሚኒስቴር መልዕክት አስተላልፏል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.