Fana: At a Speed of Life!

ካሪም ቤንዜማ ከብሄራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳዊው አጥቂ ካሪም ቤንዜማ ከብሄራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉን ይፋ አድርጓል፡፡

የ2022 ባሎን ደ ኦር አሸናፊው ካሪም ቤንዜማ በአሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕ ስብስብ ውስጥ ቢካተትም በዓለም ዋንጫው ጅማሮ ባጋጠመው ጉዳት ከውድድሩ ውጭ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ተጫዋቹ በትዊትር ገፁ ባሰፈረው መልዕክትም፥ በግሉ ለደረሰበት ስኬት ጥረት ማድረጉን ጠቅሷል።

የራሴን ታሪክ ፅፌያለሁ ያለው ቤንዜማ “የእኛ የሚለው ነገር አብቅቷል” ሲል ከብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ራሱን ማግለሉን ይፋ አድርጓል።

የ35 አመቱ ቤንዜማ ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉን ተከትሎ በቀጣይ በክለቡ ሪል ማድሪድ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል መባሉን ደይሊ ሜይል አስነብቧል።

ቤንዜማ ከጉዳቱ ጋር ተያይዞ ከአሰልጣኝ ዴሻምፕ ጋር አለመግባባት ተፈጥሯል ቢባልም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምንም ያለው ነገር የለም።

አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ጉዳቱ ቤንዜማን ያን ያክል የሚያርቀው እንዳልነበረና ለብሄራዊ ቡድኑ ተመልሶ መጫወት የሚችልበት እድል እንደነበር ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጅ በውድድሩ ጅማሮ ዋዜማ አሰልጣኝ ዴሻምፕ ቤንዜማን የቡድኑን ካምፕ ለቆ እንዲወጣ ማድረጋቸውን ተከትሎ ተጫዋቹ ቅሬታ ውስጥ እንደገባም ነው የሚገልጹት።

ቤንዜማም ወደ ኳታር ተመልሶ በፍጻሜው ጨዋታ ቡድኑን እንዲቀላቀል በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የቀረበለትን ግብዣ ውድቅ ማድረጉም የሚታወስ ነው።

ካሪም ቤንዜማ ለፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን በ97 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 37 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.