Fana: At a Speed of Life!

በጫካ የነበሩ 300 በላይ የቅማንት ታጣቂ ቡድን አባላት በሰላም እጃቸውን ሰጡ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከማህበረሰቡ አፈንግጠው በጫካ የነበሩ 300 በላይ የቅማንት ታጣቂ ቡድን አባላት በሰላም እጃቸውን ለመንግስት ሰጡ፡፡
 
ታጣቂ ሃይሎች በሀገር ሽማግሌዎች ጥረትና በመንግስት የሰላም ጥሪ ትጥቆቻቸውን ለመንግስት በማስረከብ ለውይይት መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
 
የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ÷ ታጣቂ ሃይሎች ለተጠቀሙት የሰላም አማራጭ ሒደት የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ህብረተሰብ ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ለተደረገው ጥረት ምስጋና ያቀረቡት ሃላፊው÷ከ300 በላይ የሚሆኑ ታጣቂ ሃይሎችም ወደ ቀያቸው ሰላምን መርጠው መመለሳቸው የህብረተሰቡ ስጋት የነበረውን ሞት፣ መፈናቀልና እገታ የሚቀርፍ ነው ብለዋል።
 
ቡድኖቹ አፈንግጠው በመውጣት በጠላት ሴራና በግል ፍላጎት ህብረተሰቡን በብሔር ስም እያጋጩ ለአላስፈላጊ ችግር ዳርገውት እንደቆዩ አንስተው÷ ሰርቶ መለወጥና ሀገርን መጥቀም የሚችል ወጣት ሃይልን ጫካ እንዲገባ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
 
የህወሓትን አጀንዳ እየተቀበሉ ለክፋት ሲሮጡ የነበሩ ሃይሎች በመመካከርና በንግግር መፍትሄ እንደሚመጣ ሊገነዘቡ እንደሚገባና ህብረተሰቡም ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዲመለስ ይደረጋልም ነው ያሉት።
 
የቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ኮሚቴ አበላት ችግሮች በመነጋገር እንጂ በሃይል ስለማይፈቱ የሰላም አማራጭን መቀበል ለሁሉም አካል ጠቃሚ መሆኑን በማመን መንግስት ጠርቶ እንዲያነጋግራቸው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
 
በቀጣይ መንግስት የሚያስቀምጣቸውን አቅጣጫዎች በመከተል ፊታቸውን ወደ ልማት እንደሚያዞሩም ነው የተናገሩት።
 
የሰላም አማራጩን ተቀብለው ከነትጥቃቸው የገቡ የቅማንት ታጣቂ ቡድን አባላት በመንግስት የአመለካከት ለውጥ ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል።
 
በሙሉጌታ ደሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.