Fana: At a Speed of Life!

ኮርፖሬሽኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመኖሪያና ንግድ ቤቶች ግንባታ ከኦቪድ ካምፓኒ ጋር ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክሎሎጂን በመጠቀም በሁለት የግንባታ ሳይቶች የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን ለመገንባት ከኦቪድ ካምፓኒ ጋር ስምምነት ፈጽሟል፡፡
 
ስምምነቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል እና የኦቪድ ካምፓኒ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ ተፈራርመውታል፡፡
 
ግንባታውን ለማከናወን የአልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን÷የቅይጥ አፓርትመንት ሕንጻዎቹ ግንባታ ቦሌ ኦሜዳድ እና ሾላ አካባቢ የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
የሾላ ሳይት B+G+10 የሆነ በለአራት ብሎክ ሚክስድ አፓርትመንት ሕንጸ ሲሆን÷ ቦሌ አካባቢ የሚገነባው ኦሜዳድ ሳይት ደግሞ B+G+10 የሆነ ዘመናዊ ሚክስድ አፓርትመንት ሕንጸ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
የኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል÷ኮርፖሬሽኑ ከዚህ በፊት ከኦቪድ ካምፓኒ ጋር በመሆን በ18 ወራት ውስጥ ግዙፍ የመኖሪያ መንደር እውን ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
 
ኮርፖሬሽኑ ከሚያከናውናቸው ግዙፍ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች በተጨማሪ በሌሎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰሩ መንግስታዊ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች ላይ ከኮንትራክተሮች ጋር በትብብር በመስራትና በማማከር የግንባታ ቴክኖሎጂዎች እንዲሰፉ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
 
ኮርፖሬሽኑ ያለውን የፋይናንስ አቅም መሰረት አድርጎ በተገቢው መንገድ ለመጀመር ሳይሆን ለመጨረስ በሚያስችለው አግባብ ብቻ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
 
በሾላ እና ኤሜዳድ ሳይቶች ከመኖሪያ ቤት በተጨማሪ የንግድ ቤቶችንም አካቶ የሚገነባ መሆኑንና የሳይቶቹን ግንባታም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ መታሰቡን ጠቁመዋል፡፡
 
አቶ ዮናስ ታደሰ የኦቪድ ካምፓኒ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው÷ ኮርፖሬሽኑ ጠንካራ ፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ሥርዓት ያለው በመሆኑ የሳይቶችን ግንባታ በተያዘው ጊዜ ፣ጥራት እና በጀት ለማካናወን እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል፡፡
 
ኦቪድ ካምፓኒ የሾላ እና ኤሜዳድ ሳይቶችን በከፍተኛ ጥራትና እና ፍጥነት ገንብቶ እንደሚያስረክብ ማረጋገጣቸውንም ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.