Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋና አክሱም ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ጋር ተገናኙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ እና አክሱም ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል (ግሪድ) ጋር መገናኘታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
 
ከመቀሌ-አቢአዲ-አድዋ የተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና በመጠናቀቁ የአድዋና አክሱም ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ወይም ግሪድ ጋር መገናኘታቸው ተመላክቷል፡፡
 
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የጥገና እና ቴክኒካል ድጋፍ ቢሮ
ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግስቴ እንደገለፁት÷ ትናንት ከሽረ አድዋ በ66 ኪሎ ቮልት የሥርጭት አድዋ ከተማ ኃይል ካገኘ በኋላ የአክሱም ከተማ ደግሞ በ132 ኪሎ ቮልት ኃይል እንዲያገኝ ተደርጎ ነበር።
 
ዛሬ በተከናወነው የጥገና ሥራ ከመቀሌ – አቢአዲ – አድዋ የተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና በመጠናቀቁ ከተሞቹ ሙሉ በሙሉ ከ132 ኪሎ ቮልት ኃይል ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
ይህም ሁሉም የማከፋፈያ ጣቢያዎች ከብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ጋር እንዲገናኝ ማስቻሉን ነው ሥራ አስኪያጁ የገለጹት።
 
በጦርነት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመጠገን የተጀመረው ሥራ በአብዛኛው የተጠናቀቀ ሲሆን÷ በወልዲያ ዶሮ ግብር አካባቢ የተጀመረው የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታም በመገባደድ ላይ ይገኛል ብለዋል።
 
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሃብታሙ ውቤ ÷ በጥገና ሥራው ላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ውጤት ላመጡ የተቋሙ ሠራተኞች ምስጋና ማቅረባቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.