Fana: At a Speed of Life!

ለቤት ገንቢዎች ብድር ለማመቻቸት የመዲናዋ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተፈራረመረመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ በ2005 የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ እንዲሁም ፍላጎት እና አቅሙ ያላቸውን ነዋሪዎችን በህብረት ስራ ማህበር በማደራጀት ቤት እንዲያለሙ የሚያደርገውን አማራጭ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለማስገባት የብድር አገልግሎት ለማመቻቸት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ፍላጎት ኖሯቸው የተመዘገቡ ነዋሪዎች የግንባታ ወጪውን 70በመቶ ያህል ቆጥበው 30 በመቶ ደግሞ ቢሮው ከፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦት እንደሚያመቻች ቃል በገባው ስምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር  አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑ ተገልጿል።

ቢሮው ባደረገው ጥሪ መሰረት ፍላጎት አሳይተው ከተመዘገቡት 12 ሺህ በላይ  ቆጣቢዎች  ውስጥ 4 ሺህ 580 የሚሆኑት በዳግም ምዝገባው  ተገቢውን መረጃ ይዘው የቀረቡ በመሆኑ በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ ትግበራ የሚገቡ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የተዘገቡት 4 ሺህ 580 በላይ ቆጣቢዎች 57 ህብረት ስራ ማህበራት እንዲደራጁ የመደልደል ስራ መጠናቀቁ ነው የተገለጸው፡፡

በሚቀሉት ጥቂት ሳምንታት ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ከአንድ ማህበር ወደ ሌላ ማህበር የመቀያየር ስራው ሲጠናቀቅ በህብረት ስራ ማህበር ኤጀንሲ ተደራጅተው ህጋዊ ሰውነት  እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይ ተገቢውን ቅድመ-ሁኔታ አሟልተው ህጋዊ ሰውነት አግኝተው በህብረት ስራ ማህበር ሲደራጁ ለማህበራቱ የፕሮጀክት ሳይት እና የብሎክ እጣ በማውጣት የመሬት ርክክብ  በማድረግ  ግንባታ እንደሚጀምሩም የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.