Fana: At a Speed of Life!

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በግጭት ለተጎዱ 8 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች የተሟላ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ተደርጓል-ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በግጭቱ ለተጎዱ 8 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች የተሟላ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ መደረጉን የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም ከሠላም ስምምነቱ በኋላ በሰሜን የኢትዮጵያ በነበረውን የሰብዓዊ ድጋፍ አፈፃፀም እና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም የሰላም ስምምነቱ ተከትሎ በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች በግጭት ለተጎዱ ዜጎች የሚከናወነው ያልተገደበ የሰብዓዊ አቅርቦት ሒደት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተመላክቷል።

በዚህም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በግጭት ለተጎዱ 8 ሚሊየን 358 ሺህ 196 ዜጎች የተሟላ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ መደረጉን አምባሳደር ሽፈራው ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ አጋር አካላት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፋ ለማሠራጨት ላደረጉት ርብርብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በቀጣይም የድጋፍ አሰጣጥ ሒደቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በመድረኩ በሕክምና መድሐኒቶችና በአልሚ ምግቦች አቀራረብ ላይ ተጨማሪ ጥረቶች እንዲደረጉ መጠቆሙን የኮሚሽኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

አሁን ላይ በትግራይ ክልል ብቻ 29 አጋር አካላት የሰብዓዊ እርዳታ እያሰራጬ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፥ ሌሎች በዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትም እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.