በታኅሣሥ እና ጥር ወራቶች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ለውርጭ ተጋላጭ በሆኑ ደጋማ ቦታዎች ላይ ይጨምራል – ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) በታኅሣሥ እና ጥር ወራቶች ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚያመዝኑበት ከመሆኑም በተጨማሪ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ በተለይም ለውርጭ ተጋላጭ በሆኑ ደጋማ ቦታዎች ላይ የሚያይልበት ጊዜ መሆኑን የሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
በአንፃሩ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከበልግ ወቅት መቃረብ ጋር ተያይዞ በጥቂት የሰሜን ምሥራቅ አማራ ቦታዎች ላይ ዝናብ እንደሚስተዋል ተገልጿል።
በሁለቱ ወራቶች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የትሮፒካል ፓሲፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከታኅሣሥ ወር በኋላ ቀስ በቀስ ሙቀቱ ወደ (Enso-neutral) የመሆን እድሉ እስከ 60 በመቶ ሊደርስ እንደሚችልና የህንድ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ (Neutral_IOD) ሆኖ እንደሚቀጥል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አሁን ከሚስተዋለውና ለመጨዎቹ ሁለት ወራት ከተተነተኑ የባህር ወለል ሙቀትና የከባቢ አየር ሁኔታዎች በመነሳት በአብዛኛው የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ያመዝናል ተብሏል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ በአንዳንድ የሀገሪቱ ሥፍራዎች ላይ እንደሚጨምር ይጠበቃል።
ከኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች ከሆኑት የቄለም ወለጋ፣ የጅማና የኢሉባቦር ዞኖች፣ የደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ ይኖራቸዋል ነው የተባለው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና የሲዳማ ክልሎች፣ የደቡብ አጋማሽ የሶማሌ ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖራቸው ከሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዚህ ባለፈም የበጋው ወቅት ማብቂያ አካባቢ ከበልግ ወቅት መቃረብ ጋር ተያይዞ በምሥራቅ አማራ የሚገኙ የሰሜን ሸዋ፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ይጠበቃል።