Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ የፌዴራል መንግሥት በጀት 1 ነጥብ 7 ትሪሊየን ዶላር እንዲሆን ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሀገሪቱ በጀት 1 ነጥብ 7 ትሪሊየን ዶላር እንዲሆን ረቂቅ አቀረቡ።

በኮንግረስ አባላቱ የቀረበው ረቂቅ በጀት ካለፉት አመታት አንጻር እጅግ ከፍተኛ መሆኑም ነው የተነገረው።

የላይኛው እና የተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ሣምንቱ ከመጠናቀቁ በፊት የበጀት ሠነዱን ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይመራሉም ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በጀቱ ለዩክሬን እና ለሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ (ኔቶ) አጋሮች 44 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

ተጨማሪ 40 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ደግሞ በመላ ሀገሪቷ በተፈጥሮ አደጋዎች እና ሌሎች ችግሮች ለተጎዱ ነዋሪዎች ማገገሚ እንዲውል የቀረበ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።

አመታዊ በጀት እንዲሆን ከተጠየቀው ውስጥ 858 ቢሊየን ዶላሩ ለወታደራዊ ወጪዎች እንዲውል የተጠየቀ ሲሆን፥ ይህም ባለፈው ዓመት ከተጠየቀው የ740 ቢሊየን ዶላር አንጻር ከፍ ያለ ነው ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለወታደራዊ ወጪዎች የጠየቁት የድጋፍ ገንዘብ ከዚህ መጠን ዝቅ ያለ መሆኑም ነው የተመላከተው፡፡

የዴሞክራቶች ሴናተር ፓትሪክ ሌሂ በሰጡት መግለጫ ÷ ለምገባ ፣ ለቤት ውስጥ ፍጆታ ፣ ለኃይል አቅርቦት፣ ኮሌጆችን ተደራሽ ለማድረግ ብሎም አሜሪካውያን የተጫናቸውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ ይሠራል ብለዋል።

ምናልባት በረቂቅ በጀቱ ላይ ስምምነት መድረስ ካልተቻለ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋማት ከፈረንጆቹ ገና በፊት በከፊል እንዲዘጉ ምክንያት ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው።

ከዚህ ባለፈም ሪፐብሊካኖች በፈረንጆቹ ጥር 3 ፓርላማውን ሲቆጣጠሩ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደሚችልም ነው መረጃወች የሚያመላክቱት።

“ዴሞክራቶች” እና ተቀናቃኞቻቸው “ሪፐብሊካን” ለወታደራዊ እና ለሌሎች መርሐ-ግብሮች  በሚመደቡ ድጋፎች ላይ ከሥምምነት ሳይደርሱ ለወራት ሲነታረኩ ቆይተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.