Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በፀጥታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚዋሰኑበት ቀጠና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በፀጥታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የጦር አመራሮች ቀጠናውን የሠላም እና የልማት ኮሊደር ለማድረግ እና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በጋራ ለመቆጣጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመተማ ዮሐንስ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

ከኢፌዴሪ መከላከያ ብርጋዲየር ጄኔራል ኤርቃሎ ዱካቶ÷ በድንበር አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ውይይቱ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው÷ለሁለቱ ሀገራት ሠላም መስፈን እና ልማት መረጋገጥም ውጤት ያመጣል ብለዋል፡፡

በተለይም የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ የሰዎች እና የንብረት ዝውውር በጋራ ለመከላከል ውይይቱ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የሱዳን ካርቱም አታሼ  ዋና ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል አብደላ መሐመድ በበኩላቸው÷ውይይቱ ለሁለቱ ወዳጅ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ  መሆኑን ጠቅሰው÷በቀጣይም ሂደቱን እየገመገምን ተቀራርበን ለመስራት ያስችለናል ነው ያሉት፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሠላምና ፀጥታ ምክትል ኃላፊ አቶ ጋሻው አለማየሁ በውይይት መድረኩ እንደገለፁት÷ የኢትዮጵያ እና የሱዳንን ወዳጅነት ለማደናቀፍ የሚሰሩ ፀረ ሠላም ኃይሎችን እና ሌቦችን ለመቆጣጠር ተቀራርቦ መወያየቱ የሚበረታታ ነው፡፡

በቀጣይም ሠላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ ነን ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.