Fana: At a Speed of Life!

የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በቦነስ አይረስ የጀግና አቀባበል ተደረገለት

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በዋና ከተማዋ ቦነስ አይረስ የጀግና አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

አርጀንቲና ከትናንት በስቲያ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ፈረንሳይን በመለያ ምት አሸንፋ ባለ ድል መሆኗ ይታወሳል።

የአርጀንቲና የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ቡድን ዛሬ ንጋት ላይ ቦነስ አይረስ ሲደርስ፥ ብዙ ህዝብ በጎዳና ተሰልፎ እና በደስታ ተሞልቶ ደማቅ አቀባበል አድርጎለታል።

ተጫዋቾቹ በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ የቡድኑን መለያ በለበሱ ደጋፊዎች ሆታ እና ደስታ ታጅበው ከተማውን በመዞር ደስታውን ማጣጣማቸውን የሲ ኤን ኤን ዘገባ አመላክቷል፡፡

በከተማዋ ደስታውን በጩኸት፣ በዘፈን እና ውዝዋዜ በመግለፅ የሞቀ አቀባበል ላደረገላቸው ህዝብም÷ በክፍት አውቶቡስ የተጫኑት የብሔራዊ ቡድን አባላት እጅ በመንሳት አክብሮታቸውን ገልፀዋል፡፡

አርጀንቲናውያን በምንጊዜም ኮከባቸው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ካሳኩት የ1986ቱ የሜክሲኮው የዓለም ዋንጫ በኋላ ከዋንጫው ርቀው ቆይተዋል።

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫም በኮከቡ ሜሲና የቡድን አጋሮቹ ከ36 አመታት በኋላ ቦነስ አይረስ ደርሷል።

አርጀንቲና የዓለም ዋንጫውን ከብራዚል፣ ጣሊያን እና ጀርመን ቀጥሎ ብዙ ጊዜ ማሸነፍ የቻለች ሲሆን፥ የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፏን ተከትሎ የግሏ ማድረግ ችላለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.