Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፍትህ አካላት እየመከሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፍትህ አካላት የምክክር መድረክ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ከፍትህ ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ በሚቻልበት ሂደት ላይ ምክክር የተደረገ ሲሆን ÷ በዚህም ሙስናና ብልሹ አሰራሮች በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡን እያማረሩ ያሉ ችግሮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረ ማርያም፥ ከሙስና ጋር የተያያዙ ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሄ የማያገኙ ከሆነ ህብረተሰቡ በፍትህ ተቋማት ላይ አመኔታ እያጣ እንደሚመጣ ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ ያሉ የስነ-ምግባር ችግሮችን በመቅረፍ ህዝቡ ነፃ ዳኝነትን እንዲያገኝ እየተሰራ እንደሆነም ነው የገለጹት።

የመድረኩ አዘጋጅ የ”ጀስት ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ” ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ በበኩላቸው እንዳሉት ፥ ፍትህን ለማስፈንና የህግ የበላይነት እንዲከበር የፍትህ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በርካታ የግጭት አፈታት ባህል ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ፥ እነዚህን ባህሎች በህግ በመደገፍ ፍትህ፣ እርቅና ሰላምን ማውረድ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገዛሊ አባ ስመል ተገኝተው በክልሉ ስላለው መልካም ተሞክሮ ገለፃ አድርገዋል።

በሙክታር ጠሃ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.